IRROB.ORG

Home » Miscellaneous » ሲስተር ትግስት ሩፋኤል

ሲስተር ትግስት ሩፋኤል

ጥር 15፡ 2016 ዓ. ም.

የሲ/ር ትግስት ሩፋኤል አጭር የሕይወት ታሪክ

ሲ/ር ትግስት ከአባታቸው ከካታኪስት ሩፋኤል አመዶ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ማርታ
ተክለማርያም በሰኔ 10 1975ዓ.ም በአርሲ ዞን ልዩ ስሙ ጋምቦ በሚባል ቦታ ተወለዱ፡፡ ከጥሩ
ክርስቲያን ቤተሰብ የተወለዱት ሲ/ር ትግስት በመስከረም 17 1976 የጌታችንን የኢየሱስ
ክርስቶስ ፍቅርና ምህረትን በሚያስታውሰን በመስቀል ዕለት በጋምቦ ቅድስት ስላሴ ቤ/ክ
ተጠምቀው የማርያም ወዳጅ በሆነችው በቅድስት ካቴሪን ስም ተጠሩ፡፡ እንደ ማንኛውም ካቶሊክ
ልጅ ዕድሜያቸው ተጨማሪ ሚስጢራትን ለመውሰድ ሲደርስ ተምረው ቅዱስ ቁርባንንና
ሜሮንን በዚሁ በተጠመቁበት ቁምስና ተቀበሉ፡፡

ዕድሜያቸው ለትምርት ሲደርስም በአቅራቢያው ወደሚገኘው ወደ ጋምቦ ካቶሊክ ቤተክርሰቲያን
አንደኛ ደረጃ ት/ቤት በመግባት ከአንድ እስከ 8ኛ ክፍል በዚያው ተምረዋል፡፡ ገና በሕፃንነታቸው
የመንፈሳዊ ሕይወት ዝንባሌ የነበራቸው ሲ/ር ትግስት አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጥሩ
ውጤት ካጠናቀቁ በኋላ ይህንን ከሕፃንነታቸው ጊዜ ጀምሮ በውስጣቸው የነበረውን ሲስተር
ሆኖ እግዚአብሔርን እና እርሱን ብቻ የማገልገልን ፍላጎት እዉን ለማደረግ በ1997ዓ.ም ወደ
አዲስ አበባ መጥተው ከፍተኛ 23 በሚባል ትምህርት ቤት ገብተው የ9ኛ እና 10ኛ ክፍል
ተማሩ፡፡

በውስጣቸው የነበርው ደሀን የመውደድ እና የማገልገል ብርቱ ፍላጎት ምክንያት ወደ ቅዱስ
ቪንሰንት የፍቅር ሥራ ልጆች ማህበር እንዲገቡ አስገደዳቸው፡፡ ማህበሩም በ1999 ዓ/ም ወደ        
ቦንጋ በመሄድ የፖስቱላንት ጊዜያቸውን እንዲጀመሩ አደረገ፡፡ በቆይታቸውም ባሳዩት ፍቅር፣
ብስለት፣ ትህትናና ተግባቢነት፡ በገዳሙ ካሉት መንፈሳዊ እህቶቻቸው፣ ከእኩዮቻቸው
እንዲሁም በቁምስና አባላት ዘንድ ፍቅርንና አድናቆትን አተረፉ፡፡ ይህን የተረዱት
አላፊዎቻቸውም በዚህ ትጉህ ወጣት ላይ ትልቅ ተስፋ በመጣል በታላቅ ደስታ እና ምኞት
ወደሚቀጥለው የሕንፀት ደረጃ አሳለፏቸው፡፡ ከዚያ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ለሁለት ዓመት
በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስትያን ግዳማት የበላይ ኃላፊች ጉባኤ ስር የብርሃን ፕሮገራም
መደበኛ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በመቀጠል በማህበሩ ደንብ እና ሕግ
መሠረት፡ ጥቅምት 1፡ 2001ዓ.ም የማህበሩ አባል በመሆን ለሁለት ዓመት በቅዱስ ዮሴፍ
መንፈሳዊ ሕንፀት ቤት የተመክሮ ፕሮግራም አደረጉ፡፡

ይህንን ፕሮገራም እንዳጠናቀቁ ሓምሌ15፡ 2002ዓ/ም ወደ ትግራይ ክልል አሊቴና ወደሚባለው ቦታ ለአገልግሎት ተላኩ፡፡
ሲ/ር
ትግስት ለአከባቢው አዲስ፣ ለማህበረሰቡም ቋንቋ እና ባህል እንግዳ ቢሆኑም፡ ለአከባቢው
ህብረተስብ ከነበራቸው ፍቅር፡ እንዲሁም መግባባት እና አስተዋይነት የተነሳ፡ በአጭር ጊዜ
ውስጥ የአከባቢውን ህዝብ ባስገረመ ሁኔታ የማህበረሰቡን ቋንቋ መናገር ጀመሩ፣ በዚህም ወደ
ሕዝቡም ልብ ውስጥ ጠልቀዉ ገቡ፡፡ ዛሬም ሲ/ር ትግስት በኢሮብ ሕዝብ ልብ ውስጥና
በዓዲግራት ሃ/ስብከት ትልቅ ስፍራ አላቸው፡፡ እዚያው እያገለገሉ እያሉ በፍቅር ሥራ ልጆች
ማህበር ውስጥ ሕይወታቸውን ሙሉ ለእግዚብሄር ክብር ለመኖር እና እርሱን ለማገልገል፡
የጥምቀት ቃልኪዳናቸውን በማደስ የመጀመርያ መሀላቸውን በሚያዝያ 10፡ 2007ዓም አደረጉ፡፡

ይህንን ብቃታቸውን የተገነዘበው ማህበራቸው፡ ለወደፊቱ የበለጠ ተምረው ገዳሙን፣
ሕብረተሰቡን፣ ቤተክርስትያንን እና ሀገራቸውን ያገለግሉ ዘንድ በማሰብ ወደ ኬንያ ለትምህርት
ላካቸው፡፡ እርሳቸውም ለገዳማቸው እና ለሕዝባቸው ትልቅ ህልም ሰንቀው ወደ ተላኩበት አገር
በመሄድ ታንጋዛ በሚባል የካቶሊክ ዩኒቨርስቲ በመግባት፣ በትምህርት ዘርፍ በመማር
በዲፕሎማ እና በድግሪ በከፊተኛ ውጤት ተመርቀው በ2013 ዓ/ም ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡

ለተቸገረ ሰው ሁሉ የሚሳሳ ልብ የነበራቸው ሲ/ር ትግስት፡ በአዲስ አበባ ከተማ በጣም በችግር
ከተጎዳው የህብረተሰባችን ክፍል የሚመጡት ልጆች ይማሩበት በነበረው፣ አፄ ተክለጊዮርጊስ
ካቶሊክ ትምህርት ቤት እንድያገለግሉ ተመደቡ፡፡ ይህንን አዲሱን ሥራቸውን በደስታ
ተቀበለው፣ በደስታ ብቻ ሳይሆን በወኔም ጭምር ማገልገል ጀመሩ፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት እንደ
አስተዳዳሪ ሳይሆኑ እንደ እናት፣ እህት፣ አማካሪ፣ ምስጢረኛ ሆነው ከትምህርት ቤቱ
ማህበረሰብ ጋር እያሳለፉ እያሉ፣ ቦታዉ ለልማት ይፈለጋል ተብሎ ትምህርት ቤቱ በፈረሰበት
ጊዜ ጉዳዩ እንዲስተካከል እና እነዚህ ጨቅላ ተማሪዎች እና ሠራተኞች ሜዳ ላይ እንዳይቀሩ
ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ግለሰቦች እና ተቋማትን ለማሳመን ያደረጉት ጥረት
ለሚያውቁዋቸውም ሆነ ለማያውቁዋቸው ሰዎች ምን ያህል ደሀ ወዳድ እንደ ነበሩ ያሳየ
የቅርብ ክስተት ነው፡፡

ሁልጊዜም እግዚአብሔርን በተቸገረ ሰው ለማገልገልና፣ ተምረው የበለጠ ለብዙዎች መትረፍ
የማይሰለቻቸው ሲ/ር ትግስት በአሁኑ ጊዜ ቅድስት ማርያም ካቶሊክ ትምህርት ቤት
እያስተማሩ፡ በተጨማሪም በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ዘርፍ ማስተራቸውን በወኔ
እየተማሩ ይገኙ ነበር፡፡

ሲ/ር ትግስት ባደረባቸው ሕምም በድንገተኛ ታካሚ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ጥር 14 2016
በተወለዱት በ41 ዓመታቸው እና በ15 ዓመት የአገልግሎት ዘመናቸው ከዚህ ዓለም ወደ
ዘላለማዊው አልፋዋል፡፡

ሲ/ር ትግስት ከላይ እንደተባለው ደሀን ወዳድ፤ እንደስማቸው ትግስተኛ፣ ተግባቢ፣ አስተዋይ፣
በጥሪያቸው እና በመሀላቸው በታማኝነት የኖሩ፣ በማህበራቸው የሚኮሩ፣ በአጠቃላይ ሲ/ር
ትግስት ከሰማይ የተሰጡን ውድ ስጦታ ነበሩ፡፡ ይህ ውድ ሥጦታ የሚቆይ መስሎን ነበር፡፡

ጥለውን ሄደዋል፡፡ እኛም “ጌታ ሆይ አንተ ሰጠኸን፡ አሁምን አንተ ወሰድካቸው፡ ስምህ
ለዘላለም ይባረክ” እንድንል ተገደናል፡፡

እግዚአብሔር ለሲ/ር ትግስት ዘላለማዊ ዕረፍትን ይስጣቸው የዘላለም ብርሃን ያብራላቸው፣
ለሁላችንም መጽናናትን ይስጥ፡፡

ሁላችሁም በዚህ ከባድ ሀዘናችን ወቅት ከእኛና ከቤተሰቦቻቸው ጎን ስለሆናችሁ በራሴና በፍቅር
ልጆች ማህበር ስም ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡

ሲ/ር ሕይወት ዘውደ

Weight Loss

%d bloggers like this: