IRROB.ORG

Home » Irob Related » Erobe’s values ​​in traditional theater

Erobe’s values ​​in traditional theater

የኢሮብን እሴቶች በትውፊታዊ ቴአትር

የኢሮብን እሴቶች በትውፊታዊ ቴአትር

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ትውፊታዊ ቴአትሮችን ለማዘጋጀት የብሔረሰቦችን ባህላዊ እሴቶች በሚያጠናበት መርሐ ግብር በቅርቡ ከተዳሰሱት ውስጥ የኢሮብ ብሔረሰብ ተጠቃሽ ነው፡፡ ብሔረሰቡ የሚገለጽባቸው ክውን ጥበባት ለትውፊታዊ ቴአትሩ ግብዓት ይሆናሉ፡፡ ባህላዊ አመጋገብ፣ አለባበስ፣ የፍትሕ ሥርዓት፣ ሙዚቃና ሌሎችም እሴቶች ተካተውም ብሔረሰቡ በቴአትሩ ይገለጻል፡፡ ቴአትሩ ከመዘጋጀቱ አስቀድሞ፣ የቴአትር ቤቱ የትውን ጥበባት ክፍል ባለሙያዎች ወደ ብሔረሰቡ መኖሪያ ሄደው ጥናት ሠርተዋል፡፡ ለትውፊታዊ ቴአትሩ ግብዓት የሚሆነውን ጥናት በተመለከተም ተወያይተዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በተካሄደው ውይይት ሦስት የጥናት ጽሑፎች ቀርበው፣ በብሔረሰቡ ተወላጆችና በቴአትር ባለሙያዎች አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ‹‹የኢሮብ ብሔረሰብ ትውፊታዊ ትውን ጥበባት ኢትኖግራፊክ ጥናት›› የተሰኘ ጽሑፍ በቴአትርና ትውፊታዊ ትውን ጥበባት ጥናትና ምርምር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ምትኩ በቀለ ቀርቧል፡፡ የብሔረሰቡን ታሪክ እንዲሁም አሁን የሚገኙበትን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ይዳስሳል፡፡

የኢሮብን እሴቶች በትውፊታዊ ቴአትር
የኢሮብ ሴቶች ባህላዊውን ገንፎ ሲያዘጋጁ

 

በትግራይ ክልል ምሥራቃዊ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ በሆነው ኢሮብ ወረዳ ኢሮብ ሀስበላ፣ ኢሮብ እንዳልገዳና ኢሮብ እንዳ ቡክናይት የተባሉት ተጠቃለው በኢሮብ ብሔረሰብ ይኖራሉ፡፡ የኢሮብ ብሔረሰብ የዘር ግንድ ቀዳማዊ ምኒልክ የጽዮን ማርያም ታቦትን ከእስራኤል ሲያመጡ አብረው ከመጡ ቤተ እስራኤላውያን ጋር እንደሚያያዝ ይነገራል፡፡ ከትውልድ ሐረጋቸው አንዱ ሰመ የተባለ ሰው ሲሆን፣ የኢሮብ ብሔረሰብ የዘር ግንድ አባት ይባላል፡፡

በሰሜን ከኤርትራ በምሥራቅ ከአፋር ክልል የሚዋሰነው የኢሮብ ወረዳ፣ ወደ 34 ሺሕ ሰዎች ይኖሩበታል፡፡ የብሔረሰቡ ቋንቋ ሳሆ በቅርቡ የፊደል ገበታ እየተቀረፀለት ነው፡፡ በረዣዥም ተራሮች በሚታወቀው በዚህ አካባቢ ከሚኖረው ሕዝብ አብዛኛው በእንስሳት እርባታ ይተዳደራል፡፡

ሴማዊ የዘር ሐረግና ኩሻዊ ቋንቋ ያለው ማኅበረሰቡ ውስጥ ኢሮብ ቡክናይታ የካቶሊክ እምነት፣ ሀዞ የእስልምና እምነትና የተቀሩት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ናቸው፡፡

በብዙኃን ዘንድ የሚታወቀውን የአሲምባ ተራራን ጨምሮ ብዙ ሰንሰለታማ  ተራሮች ኢሮብን ትኩረት ሳቢ አድርገውታል፡፡ በጣልያን ወረራ ወቅት ጠላትን ድል ለመንሳት እነዚህ መልክዓ ምድሮች የድርሻቸውን አበርክተዋል፡፡ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተሠራውን የጉንዳጉንዶ ማርያም ገዳም ቤተክርስቲያንን ጨምሮ ሰው ሠራሽ መስህቦችም የኢሮብ ሀብቶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት አጀማመር ታሪክ መሠረት የጣለው በ1837 ዓ.ም. የተገነባው የልደታ ትምህርት ቤትና ቤተ መጻሕፍት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡

አጥኚው እንደሚገልጸው፣ የብሔረሰቡ ባህላዊ የአስተዳደርና የግጭት አፈታት ሥርዓት ከሌሎች ማኅበረሰቦች የተለየ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ የሚተዳርበትን ባህላዊ ሥርዓት ያረቀቁት ሰባት ግለሰቦች ሲሆኑ፣ ከነፍስ ማጥፋት ጀምሮ በየደረጃው ላሉ ወንጀሎች ቅጣት የሚጣልበት ነው፡፡ አንድ ሰው ወንጀል ከፈጸመ በቁጥጥር ሥር የሚውለው በማኅበረሰቡ ትብብር ነው፡፡ በባህላዊ ግጭት አፈታቱ ቀዳሚ ቦታ የሚሰጣቸው የአካባቢው ሽማግሌዎች የጥፋቱን ክብደት በመመዘን የሚያስተላልፉት ውሳኔ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ አንድ ግለሰብ አጥፍቷል ተብሎ ከመቀጣቱ በፊት፣ በማኅበረሰቡ የተመረጡ ተወካዮች ከአካባቢው ርቀው ይወያያሉ፡፡

የአንድን ሰው ጥፋት ይመጥናል የሚል ቅጣት ሲጣል፣ ፍርዱን የሚሰጡ ሽማግሌዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች መስማማታቸው ከግምት ይገባል፡፡ በሥርዓቱ መሠረት ጥፋተኛ የሚጣልበት የካሳ መጠን ከወንጀሉ ጋር ተመጣጣኝ መሆኑም ይታያል፡፡

ኦና በመባል የሚታወቀው ባህላዊ አስተዳደር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ ቢመጣም፣ ማኅበረሰቡ ያመነባቸውን መሪዎች የሚመርጥበት ሥርዓት ነው፡፡ ብሔረሰቡ የሚመራበትን ሕግ መሠረት በማድረግ ከሚከናወነው ምርጫ በተጨማሪ የተቀሩት የማኅበረሰቡ እንቅስቃሴዎችም ይህንን መተዳደሪያ ያማከሉ ናቸው፡፡ የሚመረጠው መሪ  ማኅበረሰቡ በተገቢው ሁኔታ ያስተዳድረኛል ብሎ ያመነበት ሲሆን፣ ምርጫው የሚካሄደው ለመሪነት ከተመለመሉ ሰዎች መካከል ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ በተመረጠው ሰው ራስ ላይ ቅጠል በማስቀመጥ ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ ኃላፊነቱትን ይሰጡታል፡፡

የኢሮብን እሴቶች በትውፊታዊ ቴአትር
ደውሀን ከተማ

 

በአቶ ምትኩ ገለጻ፣ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቱና አስተዳደሩ በብሔረሰቡ ተወላጆች የዕለት ከዕለት ሕይወት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት እንደመሆኑ የከተሜነት መስፋፋት እንዳይጫነው ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ባህሉን ለመጠበቅ ስለብሔረሰቡ እሴቶች ጥናትና ምርምር ከመሥራት ባሻገር ትውፊታዊ ቴአትርን መጠቀምም ይቻላል፡፡ ከማኅበረሰቡ ውጪ ያሉ ሰዎች ስለ ባህሉ እንዲገነዘቡ ማድረግ፣ እሴቶቹ ተጠብቀው ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው የሚሸጋገሩበት መንገድም ነው፡፡

ትውፊታዊ ቴአትር ሲዘጋጅ፣ ከማኅበረሰቡ ባህላዊ እሴቶች መካከል ድራማዊ ይዘት ያላቸው ተመርጠው ታሪኩ በዙሪያቸው ይዋቀራል፡፡ መቼቱም ብሔረሰቡን በሚገልጽ መንገድ ይቀረፃል፡፡ ባህላዊ ሙዚቃ ቴአትሩ ከሚያካትታቸው እሴቶች መካከል ይገኝበታል፡፡ በኢሮብ ብሔረሰብ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያና ውዝዋዜ ጥናት ያዘጋጀው የቴአትር ቤቱ የትውን ጥበባት ጥናትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ በዛብህ ጌታሁን ነው፡፡

ማኅበረሰቡ የሚገለገልባቸው የትንፋሽ፣ የክርና የምት የሙዚቃ መሣሪያዎች በጥናቱ ተዳሰዋል፡፡ ሙዚቃ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው ቦታም ተጠንቷል፡፡ ውድድር በሚደረግባቸው ባህላዊ የሙዚቃ ሥርዓቶች ማሸነፍ፣ በኅብረተሰቡ መካከል የሚሰጠውን ዋጋ ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡ ከቆዳ፣ ከእንጨትና ሌሎችም በአካባቢው የሚገኙ ግብዓቶች ከሚዘጋጁ የሙዚቃ መሣሪያዎች መካከል ፎሪማ (ዋሽንት) እና ቱልቱላ (ከበሮ) ይጠቀሳሉ፡፡

ማኅበረሰባዊ ትስስርን ከሚያጠናክሩ ባህላዊ ጨዋታዎች መካከል ሬግዶ የተባለው የሴቶች ጭፈራና ሆራ የተባለው የትልልቅ ሰዎች ጭፈራ ይገኙበታል፡፡ በተለይ በበዓላት የዘፈኖቹ ግጥም ይዘት ይለያያል፡፡ የብሔረሰቡ ባህላዊ አለባበስ እንዲሁም ባህላዊ ምግብና መጠጥም የሚታይባቸው ሥርዓቶች ናቸው፡፡ ከፀጉር አሠረር አንስቶ ጌጣ ጌጦችም እንደ በዓላት መገለጫ ይወሰዳሉ፡፡

ኢሮብ የመስቀል በዓል ጎልቶ ከሚከበርባቸው አካባቢዎች አንዱ ሲሆን፣ ጎይዛ የተባለው ጭፈራ በበዓሉ ይዘወተራል፡፡ በጭፈራው ወቅት አዛውንቶች ረዥም፣ ወጣቶች ደግሞ አጭር ዱላ ይይዛሉ፡፡ ከበሮ እየተመታ በከበሮው ፍጥነት ልክ ጭብጨባው  እየፈጠነ ይጨፈራል፡፡ ወንዶች ነጭ ባህላዊ ልብስ ደ)()()(አዶሶራ) ሲለብሱ፣ ያገቡ ሴቶች በጋመይ ፀጉር አሠራር፣ ያላገቡ በፍኖ የፀጉር አሠራር ይዋባሉ፡፡ ባህላዊ ዘፈኖቻቸው ከሚያተኩሩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ጀግንነትን ማወደስ ተጠቃሽ ነው፡፡ ተፈጥሯዊ መስህቦቹ ማለትም የተራሮች ንጉሥ የሚባለው አይጋና አሲምባም በሙዚቃ ይወደሳሉ፡፡

‹‹የኢሮብ ብሔረሰብ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችና ጭፈራዎች የኅብረተሰቡን ባህላዊ ሀብት ያንፀባርቃሉ፡፡ ኅብረተሰቡን ስለሚያሳትፉም የሁሉንም ስሜትና ፍላጎት ያሟላሉ፤›› ሲል አጥኚው ያስረዳል፡፡ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎቹ እንዲሁም ባህላዊ ጨዋታዎቹ፣ ዘፈኖቹና ጭፈራዎቹ ለቴአትሩ ግብዓት ለማድረግ እንደሚመቹም ያክላል፡፡ በቴአትሩ ከሙዚቃ በተጨማሪ ማኅበረሰቡ የሚገለጽባቸው ሌሎች ባህላዊ ክንውኖችም ይካተታሉ፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የቴአትርና ትውፊታዊ ትውን ጥበባት ጥናትና ምርምር ከፍተኛ ባለሙያው አቶ አስታጥቃቸው ይሁን የተዘጋጀው ጥናት፣ በትውፊታዊ ተውኔት ሊካተቱ የሚችሉት የጋብቻ ሥነ ሥርዓት፣ የቀብር ሥነ ሥርዓትና አፈ ታሪክን የመሰሉ ክንውኖች ላይ ያተኩራል፡፡ ከክንውኖቹ መካከል የቅድመና ድኅረ ወሊድ ሥርዓቱን መጥቀስ ይችላል፡፡ ሴቶች ከወለዱ በኋላ የሚያጠቡት ልጅ በቂ ሙቀት እንዲያገኝና ጤናና ውበትን ለመጠበቅ የሚታጠኑበት ሥርዓት ዘመን የተሻገረ ክንውን ነው፡፡

በማኅበረሰቡ ዘንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀሩ፣ እየተለወጡ ወይም እየተቀዛቀዙ የመጡ ሥርዓቶች አሉ፡፡ ትልልቅ ሰዎች በሚሞቱበት ወቅት በጠጅ አጥቦ መቅበር ከቀሩ ባህላዊ ሥርዓቶች አንዱ ነው፡፡ በተቃራኒው ሰንደቅ ዓላማና ጠመንጃ ይዞ የትልልቅ ሰዎችን አስከሬን ማጀብ ለዓመታት የዘለቀ ሥርዓት ነው፡፡

ሉግሳ በመባል የሚታወቀው አፈ ታሪክ፣ አዳር የሚባለው የአዝማሪ ግጥምና ትነያትነ የተባለው ተረት በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ በመሸጋገር ላይ ከሚገኙ የኢሮብ ብሔረሰብ እሴቶች ጥቂቱ ናቸው፡፡ በቴአትሩ በገፀ ባህሪዎች ምልልስ ሊንፀባረቁም ይችላሉ፡፡

የኢሮብ ብሔረሰብ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ለትውፊታዊ ቴአትር ጥናት ከተደረገባቸው ዘጠኝ ብሔረሰቦች አንዱ ነው፡፡ ጥናቱን የሠሩት የቴአትር ቤቱ ባለሙያዎች በየጥናት ዘርፋቸው ለትውፊታዊ ቴአትር የሚሆኑ ግብዓቶች አቅርበዋል፡፡ ውይይቱን ከተካፈሉ ግለሰቦች ተጨማሪ መረጃዎች ለአጥኚዎቹ ተሰጥተዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎች፣ ቴአትሩ ከሌላው ማኅበረሰብ በተለየ በኢሮብ ብሔረሰብ የሚዘወተሩ ባህላዊ ክንዋኔዎችን አጉልቶ ማውጣት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በኤርትራ ውስጥ የሚኖሩ የኢሮብ ብሔረሰብ አባላት በኢትዮጵያ ከሚኖሩት ጋር ያላቸው ትስስር ምን ድረስ ነው? የሚለው ጥናት እንደሚጠይቅ ያመለከቱ ነበሩ፡፡

የኢሮብ ብሔረሰብ ተወላጆች በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ መገኘታቸው፣ የአካባቢው መልክዓ ምድርና የማኅበረሰቡ አስተሳሰብ ለነባራዊ ሕይወታቸው ያበረከተው አስተዋጽኦ በቴአትሩ መዳሰስ አለበት የሚል አስተያየት የሰጡም ይጠቀሳሉ፡፡ የኢሮብ ብሔረሰብ ድንበር አካባቢ መገኘታቸው በተለያየ ምክንያት ከኢትዮጵያ ውጪ ከሚመጡ ሰዎች ጋር በቅድሚያ የመገናኘት ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ዘመናዊ ትምህርትን ጨምሮ ለሌሎችም በዓለም አቀፋዊነት መስፋፋት ድንበር አካባቢ ለሚሻገሩ ምልከታዎች ቅርብም ናቸው፡፡

የአካባቢው ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ከጣልያን ጋር በተደረገው ጦርነት ወቅት ሳይበገሩ ለማሸነፋቸው ምክንያት ነው፡፡ የኢሮብ ስም በደርግ ወቅት ከተቀሰቀሰው ፖለቲካዊ ንቅናቄ ጋር ተያይዞም ይነሳል፡፡ ማኅበረሰቡ በልዩ ሁኔታ እንግዳ ተቀባይ መሆኑ በቀደመው ዘመን የካቶሊክ ሚሲዮናውያን ሲመጡ ከማስተናገድ ባሻገር በተለያየ ወቅት የፖለቲካ ታጋዮችን እስከ መቀበል ደርሷል፡፡

አጥኚዎቹ ከአስተያየት ሰጪዎች ከተሰነዘሩላቸው ሐሳቦች ጋር በሚጣጣም መልኩ፣ ማኅበረሰቡ በተለየ ሁኔታ ከሚያከናውናቸው ሥርዓቶች ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቱ ጉልህ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል፡፡ የማኅበረሰቡ አባላት ወደ መደበኛ የፍትሕ ሥርዓት ከመሄዳቸው በፊት ችግሮችን በባህላዊ መንገድ በራሳቸው ጥረት ለመፍታት ይሞክራሉ፡፡ አንድ ሰው ወንጀል እንደሠራ ከታመነ ከማኅበረሰቡ የተውጣጡ ሽማግሌዎች ምርመራ የሚያካሂዱበት ባህላዊ መንገድም አለ፡፡ አንድ ሰው ለፍርድ ሲቀርብ በሽማግሌዎች ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ማኅበረሰቡ አስተያየት እንዲሰጥበት ያደርጋል፡፡ ይህ የማሳተፍ ሒደት በአስተዳደር ሥርዓቱም ይተገበራል፡፡

አጥኚዎቹ እነዚህን የመሰሉ እሴቶች በዘመን ብዛትና በለውጥ ሒደት የመደምሰስ አደጋ ውስጥ መውደቃቸውን አመልክተው፣ ተጠብቀው ከሚቆዩበት መንገድ አንዱ ትውፊታዊ ቴአትሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይ የአስተያየት ሰጪዎች ሐሳብ በጥናቱ ተካቶ፣ ጥናቱ ወደ ቴአትር የሚለወጥም ይሆናል፡፡

(The Courtesy of Reporter)

 

 

Weight Loss

%d bloggers like this: