IRROB.ORG

Home » Border Issues » Voice of Irobs

Voice of Irobs

Voice and Press Release from Some Concerned Irob Group from Ethiopia in Amharic Language

Please, Note!

The following article or statement written in Amharic has very important points concerning the Irob people and their critical and unresolved geopolitical issues. However, no one should take for granted all the sacrifices the present government has taken to restore peace and security in that particular area as we all know it. Some of the positive things that are so far accomplished by and/or during the present government — such as road improvements and constructions, electrification of the area, access to some health care and immunization programs, limited telecommunication service, access to elementary and secondary education programs within the woreda, etc. — should be seen as some positive and promising accomplishments, even if they are not adequate to solve all the problems of the people of the woreda. Certainly, Irob woreda, being one of the poorest, if not the poorest in rank in entire Ethiopia as well as being terribly affected area by war, the Federal Government of Ethiopia should give more attention and some priority to the people of the area in improving their socioeconomic conditions and in addressing and solving as priority the human rights issues of those disappeared Irob peasants during the Eritrean invasion and occupation (1998-2000), as well as the peace and stability of the area without sacrificing or compromising on the woreda’s territorial integrity.

IRROB.org would be very happy to hear from the Government of Ethiopia responding to the following statement of some concerned Irobs in a constructive manner, so that everyone knows what had been and are being done to solve the existing problems of the people of the Irob Woreda from economic, developmental, educational, health, and political aspects, which have been affecting the people for a so long time. If we receive, the Federal Government’s response addressing the concerned Irobs’ legitimate and alleged reactions regarding their people and land, we will definitely post on this website for all the Irobs and other fellow Ethiopians who want to know the whole truth on all the issues affecting the Irob people who passionately and proudly claim to be always Ethiopians and remain as such forever.

As far the border-related conflict-resolutions between Ethiopia and Eritrea are concerned, IRROB.org would like to encourage and promote a peaceful and diplomatic solution versus military solution to the problem through a civilized political dialogue between the two disputing countries. After all, Ethiopians and Eritreans do not need another destructive war because they are brotherly people who can be reconciled and live in peace side-by-side as two sovereign countries.

IRROB.org
Washington, DC, USA

January 15, 2009


አዎ! ለኢሮብ ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱ የማይገሠሥ ክብሩ ነው።

የችግሩ ጥልቀት ካሳሰባቸው የኢሮብ ተወላጆች

እ.ኤ.አ 22 Dec. 2008 “Tiny Ethnic group claim Ethiopian allegiance in border row with Eritrea” በሚል ኤ. ኤፍ. ፒ (AFP) ያወጣውን ዘገባ በአንክሮ ተመልክተነዋል። ኤ. ኤፍ. ፒ የራሴ በሚለው መንግሥት ለተረሳው የኢሮብ ህዝብ ድምጽ ለመሆን በመብቃቱ ምስጋናችንን እናቀርባለን። የኢትዮጵያ ሪፖርተር ጋዜጣም፣ በጋዜጠኛ የማነ ናግሽ አማካኝነት የኤ. ኤፍ. ፒ ዘገባን ተርጕሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረቡ ምስጋናችንን ሳንቸረው አናልፍም። የህዝብ ጉዳይ የአገር ጉዳይ ነውና፣ ሪፖርተር ጋዜጣ ለወደፊቱ ለአከባቢው ይበልጥ ትኩረት በመስጠት፣ ሁኔታውን እየተከታተለ በቀጣይነት እንዲዘግብም የተማጽኖ ጥሪያችንን እናቀርብለታለን።

ከዚህ ቀጥለን ዘገባውን በመንተራስ መስተካከል አለባቸው ብለን በምናምንባቸው ጉዳዮች ላይ አጠር ያለ አስተያየት እናቀርባለን። ቀጥሎም የኢሮብ ህዝብ ብሶትን አስመልክቶ ለናሙና ያህል ከባሕሩ በትንሹ ጨልፈን ለአንባቢ ለማቅረብ እንሞክራለን።

ዘገባውን በሚመለከት

የኤ.ኤፍ.ፒ ዘገባ “ጦርነቱን ለማስቆም ይረዳ ዘንድ የኋላ ኋላ ድንበሩ በተባበሩ መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እውቅና በተቸረው ኮሚሽን ሲሰመር፣ ግዙፉን የኢሮብ መሬት ለኤርትራ እንዲሰጥ አድረጓል” (ትርጉም የኛ) ሲል፣ ሪፖርተር ጋዜጣ ደግሞ፡ “ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለውና ለኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭት እልባት እንዲያስገኝ በተመድ የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን የሰጠው የድንበር ውሳኔ አብዛኛውን የኢሮብ ህዝብ ግዛት ለኤርትራ የሚሰጥ ነው” ይላል። እዚህ ላይ ሁለቱም ዘጋቢዎች ሁኔታውን በትክክል በነበረው መልኩ ባያስቀምጡትም፣ በተለይ ሪፖርተር “….በተመድ የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን…” ያለው ትክክል አይደለም።

ምክንያቱም፣ የድንበር ኮሚሽኑን ያቋቋሙት የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ወደው፣ ተሰማምተው፣ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ዳኞችን ከመረጡ በኋላ አምስተኛ (የማኸል) ዳኛ በተመድ ተጠቁሞ እንዲቀርብና ሁለቱ ከተስማሙበት ብቻ ፀድቆ እንዲሰየም ተደረገ እንጂ ኮሚሽኑ በተመድ አልተቋቋመም። ይህም የተደረገው፣ በመሠረት- አልባው የኢትዮጵያን ጥንታዊ ግዛቶች ለኤርትራ በወርቅ ሳህን ያቀረበው፣ ሁለቱ መንግሥታት አምነው ፈቅደው በፈረሙት የአልጀርስ ስምምነት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። በተመድ የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን የሚለው አገላለጽ ተራ የቃላት ጨዋታ ሊመስል ይችላል። ሆኖም ግን በሕግ አንጻር ሲታይ ኮሚሽኑን ያቋቋመው ተመድ ነው የሚለው ድምዳሜ ላይ ከቆምን፣ የራሳችንን ችግር ለመፍታት የማንችልበት አዘቅት ውስጥ የሚከተን ይሆናል።

የሕወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት፣ የድንበር ኮሚሽኑ ብይኑን ይፋ ባደረገበት ማግስት፣ ሉዓላዊ የኢትዮጵያ ግዛት የሆነውን የኢሮብ መሬትና ሕዝብ ለኤርትራ አሳልፎ እንዲሰጥ በካድሬዎቹ አማካኝነት ሰፊ ሰበካ አካህዷል። የስብከቱና የፕሮፓጋንዳው ይዘት፤ የሄግ ፍርድ ቤት ስለወሰነብን፣ የተባበሩት መንግሥታት ስለወሰነብን፣….ወዘተ በሚሉና ከተጨባጩ እውነት ጋር ግንኙነት በሌላቸው ራስን ከደሙ ንፁሕ ለማስመሰል በተቀመሩ ድራማዎች፣ ችግሩ የተመድ እንደሆነ አስመስሎ ለማቅረብ ሞክረዋል። እውነት እንነጋገር ከተባለ ግን፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቶችን ለኤርትራ አሳልፎ የሰጠው፣ የተባበሩት መንግሥታት ወይም የሄግ ውሳኔ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ውሳኔዎች እንዲወሰኑ መንገድ የጠረገው በሁለቱ መንግሥታት ፍላጎትና ፈቃደኝነት የተፈረመው መሠረት-አልባው የአልጀርስ ውል ነው። በመሆኑም ነበር ከሕወሓት/ኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ውጭ ያሉት ኢትዮጵያዊያን ገና ከጅምሩ የአልጀርሱ ሰነድ ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ በጥልቀት በመገንዘብ፤ ሰነዱ ውድቅ እንዲደረግ በአመክንዮ የተደገፈ ጥሪያቸውንና ተቃውሞአቸውን ሲያስተጋቡ የቆዩት። የሕወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ግን ሰምቶ እንዳልሰማ በመሆን የህዝባችንን ጥቅምና አገራዊ ሉዓላዊነትን አሳልፎ ለጠላት አስረክበዋል።

የኤ. ኤፍ. ፒ ዘጋቢ ኢማኑኤል ጉጆን “….. ኢትዮጵያ የኢሮብ ህዝብን ሁኔታ እንደ አንድ ምሳሌ በመጥቀስ በያንዳንዱ ተጨባጭ ጉዳይ ድርድር እንዲካሄድ ትጠይቃለች” (ትርጉም የኛ) ይላል።

በመሠረቱ በበኩላችን መሠረት-አልባው የአልጀርስ ስምምነት እስካልተሻረ ድረስ ለኤርትራ የተቸሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች ተገቢ እልባት ስለማያገኙ በዘላቂ ሰላምና የጋራ እድገት ፋንታ፣ የማያቋርጥ የመናቆርና የጦርነት ምንጭ ሆነው እንደሚቀጥሉ የሚያጠራጥር አይደለም ብለን እናምናለን። የሕወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝም፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቶች እንደተከበሩ እንደሚኖሩና ምንም መሸበር እንደማያስፈልገን ውስጥ ውስጡን ሲሰብክ ሰምተናል፣ የሚሉ ግለሰቦች መኖራቸው ቢታወቅም በይፋ መድረክ ላይ ወጥቶ ዳር ድንበራችን እንደተከበረ ይኖራል የሚል የአገዛዙ ባለሥልጣን እስካሁን አልተደመጠም። ይህንን በሚመለከት በኢትዮጵያ መንግሥት የወጡ ሰነዶችንም ሆነ መግለጫዎችም አላነበብንም፤ አልሰማንም። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ባለ አምስት ነጥብ መደራደርያ ሓሳብም ቢሆን ስለ ኢሮብ መሬት የሚያነሳው ነገር የለም። ይባስ ብሎ ጠ/ሚ/ሩ የሰጡዋቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች የሚሉት አንድ ቤት ከሁለት እንዳይከፈል ድርድር እናድርግ ነው።

ለኤርትራ ስለተሰጠው የኢሮብ መሬት ስናወራ የኤ. ኤፍ. ፒ ዘጋቢ በትክክል እንዳሰፈረው ስለ አንድ ቤት ለሁለት መከፈል ሳይሆን፣ ስለ ብሔረ-ሰቡ ለሁለት መከፈል ነው። የአንድ ቤትና የአንድ ማሳ ጉዳይ ቢሆን ባንወደውም ይህን ያህል የሚገደን ባልሆነ ነበር። ለኤርትራ ስለተሰጠው የኢትዮጵያ (የኢሮብ) መሬት ስናወሳ ስለ አንድ ቤት ሳይሆን ተጨንቀን የምናወራው፣ ስለግዙፉ የሰሜንና የምዕራብ ኢሮብ መሬታችንና በዛው ስለሚኖረው ህዝባችን ነው። የግማሽ ያህሉ የኢሮብ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት ተገፎ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቶች ለባዕድ በተሰጡበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን እያለን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አንድም ቀን ስለ ኢሮብ መሬትና ስለኢሮብ ዜጎች አለማንሳቱ እጅጉን ይከነክነናል። ይህንን አርእስት ለማንሳት ለምን እንደሚያፍርና እንደሚፈራ ፈጽሞ ሊገባን የሚችል ጉዳይ አይደለም። ስለሆነም፣ ያስጨንቀናል፣ ያሰጋናልም። በርግጥ በብሔራዊ ክብሩ የሚኮራ የኢትዮጵያ ህዝብ ወጊድ ባይል ኖሮ፣ መንግሥት ሰጥተን እንገላገላቸው የሚል ሰበካ ከማካሄድ ባሻገር ለማተግበር መንቀሳቀሱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ዛሬም ቢሆን ህዝብ እምብየው፣ ለማንነቴ መስዋእትነቱን ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ባለበት ወቅት፣ የሕወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት ከህዝቡ ጎን ለመቆም አለመዘጋጀቱ እጅጉን ያስጨንቀናል። ለዚህም ነው የዳር ድንበራችንና እንደ ብሔረ-ሰቡ ተወላጆች የኢሮብ ህዝብ ሁኔታ የሚያሳስበን፣ የሚያስጨንቀን።

ኤ. ኤፍ. ፒ፣ ወረድ ብሎ “ኤርትራ እ. ኤ. አ በ1993፣ ነፃነቷን ከተጎናፀፈች በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት የኢሮብ ህዝብ ልብን ለማሸነፍ ከባድ ሥራ ሠርቷል” (ትርጉም የኛ) በማለት በአከባቢው ስለተከናወኑ የልማት ሥራዎች ይዘረዝራል። በመሠረቱ በመንግሥት የተከናወኑ ትርጉም ያላቸው የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል ለማለት ያስቸግራል። ቢሆንም ግን የኢሮብን ህዝብ ኢትዮጵያዊነት ጥርጣሬ ውስጥ በማስገባት ልቡን ለማሸነፍ ተብሎ የሚደረግ ልማት ከሆነ አገባብነት የለውም እንላለን። ምክንያቱም የኢሮብ ህዝብ ከጥንት ከጥዋቱ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ህዝብ ነውና። በመሆኑም የሚደረግለት ልማት ሊደረግለት የሚገባው ከዜግነት መብቱ አንጻር መታየት ይኖርበታል እንላለን።

ለመሆኑ የተከናወኑት የልማት ሥራዎች ምንድናቸው? የኢሮብ ህዝብ ቢቃወመውም፣ የሕወሓት አመራር ዳውሀንን የኢሮብ ወረዳ ርእሰ-ከተማ እንዲትሆን እንደመረጣት የሚታወስ ነው። በዚህቺው ዳውሀን (የወረዳው ርእሰ-ከተማ)- በዋናነት ከቢሮክራሲው አገልግሎት ጋር በቀጥታ የሚተሳሰሩ እንደ እስር-ቤት፣ ፖሊስ ጣቢያና የአስተዳደር ቢሮዎች የመሳሰሉ ተሠርቷል። እንዲሁም ባንዳንድ ቦታዎች ጥቂት ትምህርት-ቤቶችና ባለሙያና መድሓኒት የማይገኝባቸው በህዝብ ጉልበት የተሠሩ የሕክምና ጣቢያ ተብለው የሚጠሩ ቤቶች መኖራቸውም ይታወቃል። በዋናነት ፖሊስ፣ አስተዳደርና፣ የስለላ መዋቅሮችን ለማገናኘት የሚያስችል አንድ የስልክ መስመርም ተዘርግቷል። ከዚህ ሌላ የሕብረተ-ሰቡን የኑሮ ደረጃ ሊያሻሽል የሚችል እንዲህ የሚባል ፕሮጀክት አለ ብለን የምንጠቅሰው ነገር የለም። እኛ ልማት የምንለው ቢሮክራሲውን ማገልገል እንደ ዓላማ አርገው የሚከናወኑ ሥራዎችን ሳይሆን፣ ለህዝባዊ አገልግሎት ቅድሚያ ሰጥተው የሚሠሩትን ነው። ከዚህ አንጻር ሲታይ “ድምጺ ወያኔ” የሚዘግበውን እንመን ካላልን በስተቀር፣ በኢሮብ ወረዳ ውስጥ የሕወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት ያከናወናቸው የልማት ሥራዎች የሉም። ያም ሆነ ይህ፣ የተባለውን ያህል የልማት ተግባር ተከናውኖ ቢሆን ኖሮም እንኳ፣ እንደ የአንድ ህዝብ ዜግነታዊ መብት እንጂ፣ የአንድ ፓርቲ የልማት ክንዋኔ መመጻደቅያ ሊሆን አይገባም እንላለን።

በሌላ አነጋገር ስለ ልማት ስናወራ ከላይ የተጠቀሱት አገልግሎቶች ተጠቃሚ የሆነው ህዝብ ምን ያህል ነው? አገልግሎቱን ለመጠቀም የሚችል አቅም ያለው የአከባቢው ተወላጅ ምን ያህል ነው? አቅም እንዲኖረው ለማድረግ የተነደፉና ብዙኃኑን ለማሳተፍ የሚችሉ ፕሮጀክቶች አሉ ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ ይመስለናል። የኢሮብ ህዝብ በሻዓቢያ በተሰነዘረበት የጥፋት ጦርነት የነበረውን ሁሉ እንዳልነበረ የወደመበት መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም ግን “በጦርነት የተጎዱ አከባቢዎችን መልሶ ማቋቋም” ከሚለው መርህ ተጠቃሚ አልሆነም። በነገራችን ላይ ህዝቡ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ቀድሞ ሻዓቢያ ሊወረን እየተዘጋጀ ነው፣ በማለት አቤቱታውን ለመንግሥት ቢያቀርብም፣ በወቅቱ ሰሚ ጆሮ ለማግኘት ባለመቻሉ፣ በድንበር ጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ በየዋሻውና በየጥሻው ሲንከራተት ከሁለት ዓመት በላይ ማስቆጠሩ ይታወቃል። ጦርነቱ በተወው ጠባሳ ምክንያት እስካሁን ድረስ ወደ ቀያቸው ለመመለስ ያልቻሉ ዜጎች መኖራቸውም ገሃድ ነው። በወቅቱ ከሸዓቢያ ዓይነቱ አገር አጥፊ ጦረኛ የሚከላከልለት መንግሥት ባለማግኘቱ ህዝቡ ክላሽን ኮቭን ይዞ የሻዓቢያን ታንክና ከባድ መሳርያዎችን በዓይጋ ምድር ላይ ገትሮ በመያዝ እንደተዋደቀም ይታወቃል። በዚህ ጊዜ “ዕጡቓት ሰንበት” የሚል ስያሜ የተሰጠው ጅግናው የኢሮብ ሚሊሺያ በወራሪው ኃይል ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ የቀረውን ወደመጣበት መልሶ የነበረ ቢሆንም፣ ደጀን የሚሆነው መንግሥት ባለመኖሩ በህይወት መስዋእትነት ያስመዘገበውን ድል እንዲነጠቅ ተደርጓል። ደጀን የሚሆንለት መንግሥት ኖሮት ቢሆንና ረዳትና ስንቅ በወቅቱ ደርሶለት ቢሆን ኖሮ፣ ያ መስዋእትነት እንዳሁኑ ዋጋ ባላጣ ነበር። ሻዓቢያም ከጥቂት ቀናት በኋላ ተዝናንቶ በመመለስ አገርና ህዝብ ላይ ያንን ያህል ጥፋት የማድረስ የተመቻቸ ዕድል አይገጥመውም ነበር። ያንን ዓይነት መስዋእትነት ከፍሎ አለሁልህ የሚል መንግሥት በማጣት ድሉን የተነጠቀው የኢሮብ ህዝብ ከቀያው ተፈናቅሎ በየዋሻውና ጠሻው ቢንከራተትም መልሶ እንዲቋቋም እስከዛሬዋ ቀን ድረስ በመንግሥት በኩል የተደረገለት አንዳችም ድጋፍ የለም። ጠቅለል ባለ መልኩ ስለ ልማት ስናወራ በ18 ዓመት የሕወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ዕድሜ ውስጥ የኢሮብ ህዝብ መሠረታዊ የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል የሚያስችል የተቀየሰ ይህ ነው ተብሎ ሊነገር የሚችል የልማት ተግባር የለም።

ለኢሮብ ህዝብ ስለተደረገው ልማት፣ ስለፍትሕ መጓደል፣ ስለ የሕግ የበላይነት፣ ስለ ድንበር መካለልና በዙርያው ስላጋጠሙት ችግሮች፣ ህዝቡ ላይ ስለ ደረሱ የተለያዩ ወከባዎች፣ ስለ ሥራ አጥነት መስፋፋት፣ ስለ አከባቢው አሉታዊ የባህል ለውጥና የሚያስከትለው ውድቀት፣ የብሔረ-ሰቡን አባላት እርስ በርስ ለማጋጨት እየተሰራ ያለው አሻጥር፣ በምርጫ ’97 በገዢው ፓርቲ ያላገባብ ስለተሰረቀው ህዝባዊ ድምፅ…….ወዘተ ዝርዝር ማቅረብ የዚህ መግለጫ ዓላማ አይደለም። ባጭሩ ለማስቀመጥ ግን፣ የኢሮብ ህዝብ ተደራራቢ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ቀፍድደው ይዘውታል። በተለይ ባሁኑ ጊዜ ደግሞ በሕወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ የብሔረ-ሰቡ ህልውና ከምን ጊዜም በላይ ላደጋ ተጋልጧል።

ዘገባውን በሚመለከት ከዚህ በላይ ቆንጠር አድርገን እንዳቀረብነው ሆኖ አሁን በአከባቢው ያንጃበበው አደጋ ሥጋታችንን ከነበረው በላይ በእጥፍ እንድጨምር አድርጎታል።

ባሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደገና ወደ ጦርነት ሊያመሩ ይችላሉ የሚሉ አስተያየቶች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲሰነዘሩ ይሰማል። የኤ. ኤፍ. ፒ ዘጋቢም የሚጠቁመው ይህንኑን ነው። የአፍሪቃ ቀንድ ያለመረጋጋት ሁኔታም አከባቢው የሰላም ቀጠና ሊሆን የሚችልባቸው ፍንጮችን በማሳየት ፈንታ የሰላም ፍላጎታችንንና ተስፋችንን የሚያጨልም ደመና እያንጃበበበት ይገኛል። የኤርትራ መንግሥትም የጠብ ተንኳሽነቱን የሚያቆም መስሎ አይታይም። የመለስ ዜናዊ አገዛዝም የአገዛዝ ዕድሜን ይጨምርልኛል ብሎ ካመነ፣ ሁኔታውን ሊጠቀምበት እንደምችል ጥርጥር የለውም። እነ ግብፅና ሱዳን ጥቁር ዓባይን አስመልክቶ የራሳቸው የረጅምና አጭር ጊዜ እቅድ አላቸው። የአገር ውስጥ ሰላማችንም ባስተማማኝ መሠረት ላይ የቆመ አይደለም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሁነን አሁን ጦርነት ቢጀመር ዛሬም እንደገና ከ80 ሺ በላይ የዜጎች ሕይወት የሚቀጥፍ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። ይህንን ሁሉ ደማምረን ስንገመግም የኢሮብ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ያሉ ዜጎቻችን የሚከፍሉት መስዋእትነት ከፍተኛ እንደሚሆን ግምት ውስጥ እናስገባለን።

እንደ ከዚህ በፊቱ፣ ዛሬም “ሳናውቀው” ልንወረር እንደምንችል መጠርጠሩ አይከፋም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የኢሮብ ህዝብ ከማንም በላይ ተጎጂ ሊሆን እንደሚችል የማያጠራጥር ሃቅ ነው። ከዚህ በፊት በሻዓቢያ ተጠልፈው የተወሰዱት ከመቶ በላይ የኢሮብ ዜጎችን የት ደረሱ ብሎ የጠየቀ የመንግሥት አካል የለም። የኢትዮጵያ መንግሥት ከዳሎል ተጠልፈው የተወሰዱት የፈረንሳይና የእንግሊዝ ዜጎች (ቱሪስቶች) ለማስፈታት ሲል ያካሄደው ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ የሚደነቅ ከመሆኑም በላይ ውጤትም አስመዝግቦ ቱሪስቶቹ መፈታታቸው ይታወሳል። ከ10 ዓመት በፊት በሻዕቢያ ስለተጠለፉትና እስካሁን ድረስ መዳረሻቸው የማይታወቅ ከ100 በላይ ኢትዮጵያዊ የኢሮብ ተወላጆች ግን ዲፕሎማሲያዊ ግፊቱ ይቅርና የውግዘት መግለጫም በመንግሥት በኩል አለመሰጠቱ እጅጉን አሳዝኖናል። በመሆኑም ህዝባችን ቁርጥ ቀን ሲመጣ ከራሱ ውጭ ሌላ ድጋፍ እንደሌለው ቆጥሮ መንቀሳቀስ የህልውናው ብቸኛ ዋስትና መሆኑን ተገንዝቦ ራሱን ለመከላከል አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል። በበኩላችን ህዝቡ በራሱ ተደራጅቶ በሚወስደው ማነኛውም እርምጃ ላይ ከጎኑ እንደማንለይ ልናረጋግጥለት እንወዳለን። ከዚህም በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች፤ እንዲሁም ለሃገር መከላከሊያ ሠራዊት የኢሮብ ብሔረ-ሰብን የገጠመው አሳሳቢ የመኖርና ያለመኖር ሁኔታን ግምት ውስጥ በማስገባት ደህንነቱና ህልውናው የሚጠበቅበት ሁኔታን እንዲከታተሉና ባስፈለገ ጊዜ ሁሉ እንደ ከዚህ በፊቱ አሁንም ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ኢትዮዽያና ህዝቧ ለዘላለም ይኖራሉ!!!
የኢሮብ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት በማንም ኃይል አይገሰስም!!!

Weight Loss

%d bloggers like this: