IRROB.ORG

Home » Border Issues » Right to Exist » Irob Diaspora Statement (Amharic)

Irob Diaspora Statement (Amharic)


ሰኔ 2010 ዓ.ም. 

በአልጀርስ ውል መሰረት በሄግ የተወሰነው የድምበር ማካለል ውሳኔን አጥብቀን እንቃወማለን!

እኛ ከአገራችን ውጭ በተለያዩ ክፍለዓለማት በስደት የምንኖር የኢሮብ ተወላጆች፣ በግንቦት 28 2010 ዓ.ም. የኢህአዴግ  ስራ አስፈጻሚ ሲያካሄደው  የሰነበተበትን ስብሰባ በኢትዮጵያና ኤርትራ  መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የአልጀርስን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ዝግጁ መሆኑን፣ በመግለጽ የሰላም ጥሪ ማቅረቡ እጅጉ አሳዝኖናል አስቆጥቶናልም። ስለሆነም የኢሮብ ብሄረሰብ በተለይ በሃገርቤት በወረዳው ርእሰ ከተማ በዳውሃን የጀመረውን ሰላማዊ ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባዎች አማካኝነት ተቃውሞውን በመግለጽና አቤቱታ በማቅረብ ላይ ይገኛል።

እኛ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ነዋሪ የሆን የኢሮብ ተወላጆችም ይህ በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ የተላለፈው አደገኛው ሳኔ በህልውናችንና በሉዓላዊነታችን ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ እጅጉን አስቆጥቶናል። በመሆኑም፣ ሰኔ 2 ቀን 2010 ዓ.ም አስቸኳይ ተለኮንፈረንስ በመጥራት ዓለም-አቀፍ የኢሮብ ተወላጆች ስብሰባ አካሂደናል። በተካሄደው የስልክ ስብሰባም የሚከተሉትን ወሳኔዎች አስተላልፈናል፣

1.አገርቤት የሚካሄደውን ሰላማዊ የኢሮብ ህዝብ እንቅስቃሴ በሃሳብ፣ በንዋይ፣ መሞራልና በዲፕሎማሲ ሥራዎች አቅም የሚፈቅደውን ሁሉ በማድረግ መደገፍና ማበረታታ፣

2.የሃገር ቤቱን ሰላማዊ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ለመደገፍ በየክፍለ ዓለሙ የሚኖሩ የኢሮብ ተወላጆችን ማስተባበርና የህዝባችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲደግፉ ማበረትታታት፣

3.የአልጀርስ ሰምምነት የ1900፣ 1902 ሆነ 1908 እ.ኤ. አበ አፄ ሚኒልክና ጣሊያን መንግሥት መካከል መተደረገው ስምምነት መሠረት  እንዲካለል ሁለቱ ባለጋራዎች የተሰማሙ ስለሆነና ኢሮብም በነዛ ውሎች መሠረትም ቢሆን በጣሊያን አስተዳደርም ሆነ  ቅኝ ግዛት የሆነበት ታሪክ ስለሌለ ጥያቄ ውስጥም መግባት ያልነበረበት በመሆኑና ይልቁን ጣሊያን በ1935 ዓምፈ ኢትዮጵያን ሲወርም ኢሮብን ይገዛ የነበረው ከሰንዓፈ ወይም ከሌላ በቅኝ ግዛት ይዟት ከነበረችው የኤርትራ ክፍለሃገር ሳይሆን ከዓጋመ አውራጃ ከዓዲግራት በሚሾሙ ገዢዎች ነው የነበረው። ይህ ኢሮብ የኤርትራ አካል ሁኖ እንዳማያውቅ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል ጭብጥ ነው። በሌላ በኩል ያ ውል ይጸናል እንኳ ቢባል ኢሮብን የማይመለከት ከመሆኑም በላይ ጣልያን በ1935 ዓ.ም.ፈ ኢትዮጵያን ሲወር የፈረሰ በመሆኑ ኢትዮጵያ በውሉ የመገዛት  ግዴታ  የለባትም። ስለሆነም በዚህ በፈረሰ ውል የተፈረመው የአልጀርስ ውልና በዛ ውል መሠረት የትቋቋመው ኮምሽን የሰጠው ብይን ፍትሓዊ ባለመሆኑና የኢሮብ ህዝብን ለሁለት በመክፈል ህልውናችንን የሚያጠፋ በመሆኑ፣

4.የኢሮብ ህዝብም ሆነ የኢሮብ መሬት በኢጣሊያ ጊዜም ሆነ ከዛ በፊትም ሆነ በኋላ የኤርትራ አካል ሆኖ የማያውቅ በመሆኑ፣ ኤርትራ ነፃ ወጣች የተባለ ጊዜም ቢሆን የኤርትራ መንግሥት ወረዳችንን ረግጦ ባለ ማወቁና ከኤርትራ ነፃነት በኋላም ሆነ በፊት ኤርትራ በሚባል ክፍለገር ሥር አንድም ቀን በኤርትራ ተዳድሮ የማናውቅ በመሆኑ፣ የኤርትራ መንግሥት ዓለም-ዓቀፍ እውቅና ተችሮት በ1993 ዓ.ም.ፈ ሪፈረንዶም ሲያካሂድም ኢሮብ የኤርትራ አካል ሆኖ እንደማያውቅ ጠንቅቆ በማወቁ ሪፈረንደም እንዲያካሂድ እንኳ ባለመጠየቅ ግዛቱ እንዳልሆነ ያመነ  በመሆኑ፣

5.ይህ በአልጀርስ ውል መሰረት በሄግ ውሳኔ ለኤርትራ የተሰጠው ሉዓላዊ የኢትዮጵያ መሬት በ1990 ዓም በሻዕቢያ በተወረረበት ጊዜ በመጀመሪያ የኢሮብ ህዝብ ቀጥሎ ደግሞ አእላፍ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረ-ሰብ ልጆች ወራሪውን የሻቢያ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ለማባረር ባካሄዱት እልህ አስጨራሽ ጦርነት ደማቸው የፈሰሰበትና አጥንታቸው የትከሰከሰበት መሬት በመሆኑ፣

6.በአልጀርሱ ውል መሰረት ድንበር እንዲያካልል የተቋቋመው ኮሚሽን በ1995 ዓ.ም ውሳኔውን እንዳሳወቀ የኢሮብ ህዝብ ውሳኔውን በይፋ በመቃወም ከዞባ አስተዳደር ጀምሮ ለትግራይ ክልል መንግስት፣ ለትግራይ ክልል ፓርላማ፣ በፈደራል  ደረጃ ለራሳቸው የውሉ ዋና ፈራሚ ለነበሩ ለሟች ጠቅላይ  ሚንስተር አቶ መለስ ዜናዊ፣ በወቅቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስተር ለነበሩ ለአቶ ስዩም መስፍን፣ ለፈደራል መንግስቱ ፓርላማ፣ ለአፍሪካ ህበረትና ለተባበሩት መንግስታ ተቃውሞውን በጽሁፍ ቢያቀብም ሰሚ ሳያገኝ ተንጠልጥሎ የቆየ በመሆኑ፣

7.የኢሮብ ብሄረ-ሰብ እንደ ብሄረ-ሰብ ከሚታወቅበት ረጀም ዘመናት ጀመሮ አንድም ቀን ኤርትራ ከምትባል ክፍለሃገር በጉርብትና ካልሆነ በስተቀር በአስተዳደር ስርዓት ተገናኝቶ የማያውቅ  በመሆኑ፣ ኤርትራ ከናቷ ከኢትዮጵያ ተለይታ ለ60 ያህል ዓመት በጣልያን ባእዳዊ አገዛዝ ሥር በቆየችበት ጊዜ ጣሊያን ከሰንዓፈ እየተነሳ የኢሮብ ወረዳን ሊቆጣጠር ሲሞክር የኢሮብ ህዝብ ገና ደንበሩ ላይ ጠብቆ ድባቅ እየመታ ወደ ቦታ እንዲመለስ አደረገው እንጂ ጣሊያን የኢሮብ ወረዳን ያልረገጣት በመሆኑ፣ የኢሮብ ህዝብ  ከጥንት ጀመሮ የሚያስተዳድሩትን በነፃነት ራሱ መርጦ ኦና በሚል መዓርግ እየሾመ ራሱን የሚተዳደርበት ሥርዓት የነበረው፣ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ በትግራይ ከፍለ ሃገር ስር ሲተዳደር ኖረ እንጂ አንድም  ቀን ከኤርትራ ጋራ የሚያቆራኘው አስተዳደር ኖሮትባለማወቁ፣

8.አቶ መለስ በጦርነት የተሸነፈው ሻዕቢያን አልጀርስ ድረስ በመጐተት የተዋዋሉት ውልና በዚህ ውል መሰረት በሄግ ተሰጠው ውሳኔ በኛ በኢሮቦች እንደ አንድ በሃገርና በህዝቦቿ የተፈጸመ ደባ የሚቆጥረው በመሆኑ፣ ይህ የክህደት ውልና ውሳኔ በቀርቡ የጠቅላይ ሚንስተርነት ቦታ ተረክበው በገዥው ፓርቲ ደብዝዞ የነበረው ኢትዮጵያዊነት ላይ ነብስ እየዘሩ ባሉበትና በገዥው ፓርቲ ምክንያት በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ጥላቻና የርስበርስ ጥርጣሬ በማከም በርካታ ስራዎች በመስራት ላይ ባሉበት አንድ ኢትዮጵያዊነት ከጥንት ጀመሮ ከደሙ ጋራ የተዋሃደ የኢሮብ ህዝብ እጅግ ከፍተኛ ተስፋ በጣልንባቸው በተከበሩ ዶከተር ዓብይ ኣሕመድ አፍ ያ የአቶ መለስ የክህደት ውልና በውሉ መሰረት የተደረገው ውሳኔ እንዳለ ተቀብለን ለተግባራዊነቱ እንንቀሳቀስላን ሲሉ መስማት አስገራሚም አስደንጋጭም ሆኖ ስላገኘነው፣ ዶ/ር ዓብይ መጀመሪያ ሲመረጡ፣ በፓርላማ ለኢትዮጵያ ህዝብ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮ-ኤርትራ ችግር በውይይት ለመፍታት እሰራለሁ፣ ሲሉን ተስፋ ያደርገነው ለመፍትሄው ከኤርትራ መንግስት ጋራ ከመነጋገራቸው በፊት፣ ጉዳዩ የሚመለከተውን ህዝብ ያነጋግሉ ብለን ስንጠብቅ፣ ያ የተለመደው መሪዎች ከራሳቸው ጋራ ብቻ ተነጋግረው ህዝቡን ያላሳተፈ ውሳኔ እጅግ ከፍተኛ ተስፋ ባሳደርንባቸው ክቡር ዶክተር ዓብይም ሲደገም፣ በሳቸው ላይ የነበረን ተስፋ እጅግ ያጨለመብን በመሆኑ፣

9.በኢሮብ ህዝብ እምነትና በዓለም-ዓቀፍ የሕግ መስፈርት ሲታይ፣ ኤርትራ አስቀድማ የአልጀርስ ውልንና የሄግ ወሳኔ ድንጋጌ የሆኑትን የጊዜአዊ የፀጥታ ቀጠና በመጣስና የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከሪ ኃይል በማባረር ስምምነቱን ያፈረሰችው በመሆኑና ሁሌ ነገሮች ኤርትራ እንደፈለገችውና እንደተመኘችው ለማድረግ  የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚያስገድደው ሕግ እንደማይኖር የምንገነዘብ በመሆኑ፣

10.መጀመርያውኑ ኤርትራ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ መሬት ስትወር የመሬት ወረራው በኢትዮጵያ ውስጥ የነበራትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ለማስከበር ለመደራደሪያነት እንጂለ መሬት ባለቤትነት እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ከላይ እንደጠቀስነው ለመሬት ባለቤትነት ቢሆን ኖሮ በ1993 ዓምፈ ነፃነት ወይ ባርነት በሚሊ ኤርትራ ውስጥ በተካሄደው “ህዝባዊ ረፈረንዶም” እነዚህ አሁን በባለቤትነት የምትከራከርባቸው አከባቢዎች ላይም ለማካሄድ ትሞክር ነበር። አላደረገችውም። ስለሆነም ይህ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ለጦርነት መንስኤ ስላልሆነ የተፈለገውን ያህል መሬት ቢሰጣት ሰላም ለመፍጠር ዝግጁ ለመሆን የማትችል በመሆኑ፣

11.በሁለቱ ሃገሮች ህዝቦች መካከል ካስፈለገ ድንበር ተከልሎ እውነተኛ ሰላም እንዲፈጠር ፍላጎቱ በሁለቱም መንግስታት በኩል ካለ በሁለቱ ሃገራት ጠረፍ በየአከባቢው የሚኖር ህዝብ ድንበሩን ራሱ በስምምነት ከልሎ ለሁለቱ መንግስታት ለማሳውቅ ችሎታውም ፍላጎቱም እንዳለው በሚገባ ስለምናውቅ፣ ስለሆነም፣ ከጅምሩ ጀምሮ የተሳሳት መንገድ በመከተል ለተበላሸው ጉዳይ የኢሮብ ህዝብ ባልዋለበት የገፈቱ ቀማሽ መሆን ስለሌለበት፣ በዚህ የተሳሳተ ውል መሰረት በደረገው ብይን የኢሮብ ህዝብን ለሁለት በመክፈል ህልውናው አደጋ ውስጥ መግባት ስለሌለበት የኢህአዴግ ስራስፈጻሚ በግንቦት 28 2010 ዓ.ም. ያወጣውን መግለጫ አጥብቀን እንቃወማለ፣ በሃገርቤትም በዲያስፖራም የምንኖረው የኢሮብ ብሄረሰብ ኣባላት ለህልውናችን ባንድነት እስከመጨረሻው እንታገላለን፣ ሁሉም አገር-ወዳድ ኢትዮጵያዊም ከጎናችን እንዲሰለፍና ለህልውናችን የምናደርገውን ሰላማዊ ትግል በቻለው ሁሉ እንዲረዳን የከበረ ጥሪያችንን እናቀርባለን! የኢሮብ ብሄረሰብ ለሁለት አይከፈልም!!!በተለያዩ ክፍላተ ዓለማት የሚንኖር የኢሮብ ተወላጆች ሕብረት፣ ከኛ ጋራ ለሚደረገው ግኑኝነት irobcomm@gmail.com አማካይነት መገናኘት ይቻላል።  

Image may contain: 6 people, outdoor

 

Weight Loss

%d bloggers like this: