Advertisements
IRROB.ORG

Home » አስተያየቶች » ጥላቻ ይቅር

ጥላቻ ይቅር

የአባ ተስፋማርያም ባራኪ አስተያየቶች

ጥላቻ ይቅር

እባካችሁ ስለ እግዚአብሔር፣
ጥላቻ ይቅር፤
እርቅና ፍቅር፣
ከሰላም ጋር፣
ይበጃል ለአገር፤
ከመኰራረፍ መነጋገር፣
ይከፍታል በር፣
ያስችላል ለመከባበር፣
መፍትሔ ይገኝለታል ለነገር፣
ያደርሳልም ወደ ትብብር፣
ይፈታልም ሁሉን ችግር።


ዕውር ጥላቻ

ባለበት ዕውር ጥላቻ፣
ይነግሥበታል ሰይጣን ብቻ፤
ሳይኖረው ከእግዜር አቻ፤
ያሸንፋል የሌለውን መመከቻ፤
እየከሰሰ ሁሉን ያለ መረታቻ፣
እያደረጋቸው የክፋት መተቻ፤
ያወርዳል ወደ ስቃይ መከማቻ፤
ያ ቦታ የለውም መክፈቻ፣
የዘላለም እስር ቤት የክፉዎች መክተቻ።


ጥላቻ ባለበት

ጥላቻ ባለበት ስፍራ፣
መስማማት አይቻል ከሰው ጋራ፤
ተንኰል ሁሉ እየተሠራ፤
ያደርሳል ወደ መጥፎ ኪሳራ፤
ይኸ ሁሉ የሰይጣን ሥራ፤
ስለሚጠላ ባለ እንጀራ፣
ስለማይወደድ ባለጋራ፣
ስለተረሳ የእግዜር አደራ፤
ሰው ከሰይጣን እየተጋራ፣
ኑሮው ይሆናል መራራ፣
ለባለጋራው ስለማይራራ፣
በጥላቻ እየነደደ እንደ ዳመራ፤
በሕይወቱ ብርሃን ስለማይበራ፣
ዕረፍት እንዳጣ አሞራ፣
ሲበርር ይኖራል ከስፍራ ወደ ስፍራ፣
ወደ ዘላለም ጥፋት እስኪያመራ።


ጥላቻ በጣም አደገኛ

ጥላቻ ለሰው በጣም አደገኛ፣
ያደርግሃል የመንፈስ በሽተኛ፣
የልብ ሕመምተኛ፣
በመንፈስ ጭንቀተኛ፣
በአምላክ ፊት ኃጢአተኛ፣
በሰው ፊት ደመኛ፣
የዲያብሎስ ጓደኛ፣
ሁልጊዜ ኀዘንተኛ፣
በሌሊት የማይተኛ፣
የሰው ቍጠኛ፣
የቂም እስረኛ፣
የዓለም ተንኰለኛ፣
የሰው ብቸኛ፣
የማይሆን ደስተኛ፤
ለኅብረተሰብ ጠንቀኛ፣
ለአንድነት መርዘኛ፣
ለፍቅር ሁሉ ምቀኛ፣
ጸጋ የጎደለው አበሰኛ፣
አታላይ አፈኛ፣
ከሓቅ የራቀ ውሸተኛ፣
ራሱን የሳተ እልኸኛ፣
ሰውን የሚያጣላ ወገነኛ፣
የማይታመን ከዳተኛ፣
እየመሰለ የአገር አርበኛ፣
እየታየ እንደዓለም ዳኛ፣
ንጹሑን እያለ አንተ ወንጀለኛ፣
እያስመሰለው መጥፎ ግፈኛ፣
ሰውን ያጣላል ክፉኛ።


ጥላቻ የሰይጣን መሳሪያ

ጥላቻ የሰይጣን መሳሪያ፣
የሰው ዘር ማጥፊያ፣
ለሰይጣን ተከታዮች መመኪያ፣
ኤረ ይጥፋ ወዲያ፣
ከሀገራችን ኢትዮጵያ፤
ይዘመርለት ለፈጣሪ ሃሌ ሉያ፣
ይሰገድለት ለርሱ በቅድሚያ፣
እርሱ ነውና ሁሉን የፈጠረ መጀመሪያ።
ምን ነው ወገኖች ታዲያ፣
ሆኖ መቅረቱ የዓለም መሳለቂያ፣
ለጠላቶች መሳቂያ፣
ለዲያብሎስ መኵሪያ፣
ወደ ገሃነም የሚመራ በጥድፊያ፣
የሚያስከለክል የሰማዩን መኖሪያ።


ጥላቻ ላመጣ ጣጣ

ጥላቻ ላመጣ፣
ታላቁ ጣጣ፣
የኃጢአት ፈንጣጣ፣
መድኃኒቱ ታጣ፤
ሰው ከዚህ እከይ ካልወጣ፣
ይወርዳል የእግዜር ቍጣ፣
እንደ እሳት እየተንጣጣ፣
ሰውን ሊቀጣ፣
የጥላቻን መርዝ የጠጣ፣
ይረግፋል እንደ አንበጣ፣
ደርሶበት የዘላለም ሞት ዕጣ።


በጥላቻ ሰበብ

በጥላቻ ሰበብ፣
ያልቃል ብዙ ሕዝብ፣
በጥይትና ቦምብ፣
እየረገፈ እንደ ዝንብ፣
ስለሚራቅ ከእግዚአብሔር አብ፣
ይቅር ስለማይባል ከልብ፤
ሰው እየገነባ የጥላቻን ግንብ፣
የጠላውን በመክበብ፣
እንዲጥል ወደ ግብ፣
ሁልጊዜ እንደተዘጋጀ ለጠብ፤
ኋላም እየተማረከ ለገንዘብ፣
እየጣሰ ሕግንና ደንብ፣
ይሆናል እስግብግብ፣
አይደርስምም እግብ።


ጥልቻ ያደርጋል ሰውን እንስሳ፣
የፈጣሪንም ሕግ እንዲረሳ፣
እንዲኖርም በኃጢአትና አበሳ፤
ለኅብረተ-ሰብ ክፉ ነቀርሳ፣
ጨርሶ የሌለው የኅሊና ወቀሳ፣
ሰውን የሚመርዝ ሰላምን እየነሳ፣
አሉታዊ ነገርን ብቻ እያወሳ፣
ይቀሰቅሳል በሀገር ጦርነት እንዲነሳ፣
ወገንን ያነሳሳል ለወገን ድምሰሳ፣
ጥላቻ እውነትም ክፉ አበሳ፣
ሰውን የሚለውጥ ወደ አውሬ እንስሳ።


ጥላቻ የፖለቲካ አለንጋ፣
የሚበታትን አንድን መንጋ፣
አጥንትን ሰብሮ ልብን ይሚወጋ፣
አያስተኛ በበቀል ፍለጋ፤
እንቅልፍ የሚያሳጣ ሌሊቱ እስኪነጋ፣
ፍቅርን የሚያደርቅ እንደ በጋ፣
ላንድ ሕዝብና ሀገር ትልቁ አደጋ፣
ሰውን ያስጨርሳል እያዋጋ፣
ወገኖችን እያፋጀ ከኤርትራ እስከ ወለጋ፣
ሁሉን እያራቀ ከእግዚአብሔር ጸጋ፣
እንደዚሁ ይጠፋል ሰው ነፍሱን እየዘነጋ፣
ከፈጣሪ ይልቅ ወደ ሰይጣን እየተጠጋ፣
መንፈሱ ተረብሾ ልቡ ሳይረጋ፣
ሁሉን ባዶ ያስቀራል ያላንዳች ዋጋ፣
ነፍሱ በክፋትና ንዴት ስለተወጋ፣
በፍራት ብቻ ይኖራል ወትሩ እየሰጋ።


ጥላቻ ምንም የለውም ፍሬ፣
ሰውን ከመለወጥ በቀር ወደ አውሬ፣
ውስጥን እያቃጠለ እንደ በርበሬ፣
ሰላምን ይነሳል እንደ ተዋጊ በሬ፣
ስምን በማጥፋት በሐሰት ወሬ፣
ዋና መሳሪያ ነው ለሰይጣን አጅሬ፣
መንግሥትንም ለማጋጨት ከድሃው ገበሬ፣
በፍጹም አይበጅም ለኢትዮጵያ ሀገሬ።


ሰው ከተመረዘ በጥላቻ፣
ይገባል ከሰይጣን ጋር ጋብቻ፣
ሌት ተቀን የሚያስበው እከይን ብቻ፣
የጠላውን ለማጥፋት በበቀል ዘመቻ፣
ሆኖ ይቀራል የዲያብሎስ ኰረቻ፣
እፎይታ ሳይኖረው በስጋትና ፍራቻ፣
በንዴት እየተቃጠለ እንደ ጕልቻ፣
ለብስጭቱ አይገኝለትም መፍቻ፣
ለውስጣዊ ኀዘኑም የለውም አቻ፣
ያምላክ ጸጋ ስለሚጐድለው ለመበረታቻ።


በጥላቻ ሰው ተፋጀ፣
ሆኖ ሳለ በክርስቶ ደም የተዋጀ፣
ለራሱ የጥፋትን መንገድ አበጀ፣
ከዲያብሎስ ጋራ እየተወዳጀ፣
በተንኰልና ክፋት ብቻ አረጀ፣
በማይረባ ፖለቲካ እየተደራጀ፣
ሁሉን በውሸት እየፈረጀ፣
ወገን ከወገን ጋር እያፋጀ።


ጥላቻ ምንም የለውም ፋይዳ፣
በአምላክ ፊት ግን ትልቁ ዕዳ፣
ለዘላለም ነፍስን የሚጐዳ፣
የሚያደርግህም የዲያብሎስ እንግዳ፣
የሚያወርድብህም የኵነኔን ፍዳ፣
በሰው ዘንድ የሚያደርግህ ወራዳ፤
ሰው እርስበርስ እንዳይረዳዳ፣
ሁሉን ያሸሻል ወደየ ጓዳ፣
ያስቈጥራል እንደ አንድ ቡዳ፣
ለም መሬትን የሚያደርግ ምድረበዳ።
የጥላቻ ፍሬ ይህ ከሆነ ዘንዳ፣
ምን አለበት ወገን ሁሉ ከባሌ እስከ ባዳ፣
ጥላቻን ትቶ በፍቅር ቢረዳዳ፣
ሰላም በሰፈነ በሁሉም ወረዳ።


በሰው ልብ ጥላቻ ካደረ፣
ሰው በሰይጣን ሰንሰለት ታሰረ፣
የእግዜር ብርሃንን ከማየት ታወረ፣
በሁሉም ነገር እየተማረረ፣
ሌሊቱን ሲሰቃይ ብቻ አደረ፣
ሰው ፍቅርን ካልተማረ፣
ምንም’ንኳ ቢመስለው ለሀገሩ የተቈረቈረ፣
ሆዱ በጥላቻና ንዴት እያረረ፣
ሥራው ከንቱ ይሆናል ለማንም ያላማረ።


ጥላቻ ለደግ ሰው እንደ እሬት መራራ፣
ክፉ ሰውን ግን ያስመስላል ጠንካራ፣
የእግዚአብሔርን ሕግ ስለማይፈራ፣
የሰይጣንን ሥራ ስለሚሠራ፣
በጦር ሜዳም ስለሚሰማራ፣
በደካማው ላይ እያጕራራ፣
ሌላውን በጠበንጃ እያስፈራራ፣
በጥይት ኃይል ብቻ እየኰራ፣
ሌላውን እየቈጠረ እንደ አቧራ፣
እራሱን ግን እንደ ሊላ አሞራ፣
የማይደክም በሰማዩ በረራ፣
በደካማው ፍጥረት እየፈጸመ ወረራ፣
አይገታም ከሰይጣን ሥራ፣
አምላክ እስከሚጥለው ወደ ዘላለማዊ እሳተ ጎሞራ።


ጥላቻ ጠንቅ ነው ለነፍስ፣
የሰውን ልብ የሚያረክስ፣
በእግዜር ፊት የሚያስከስስ፣
ሰላምን በማደፍረስ፣
ጥልን በማንገሥ፣
ክፉን በመወደስ፣
ጻድቁን በመውቀስ፣
ያስጠጋል ወደ ዲያብሎስ፣
ያርቃል ከቅዱስ መንፈስ፣
ጸጋን በማስጨረስ፣
ጽድቅን በመደምሰስ፣
ለዘላለም ለማስለቀስ፣
ፍጻሜ በሌለው ቀውስ፣
ያላንዳች ፈውስ፣
ያስኰንናል የሰውን ነፍስ።


ሐዋርያው ዮሐንስ እንዳለ፣
የባለእንጀራን ፍቅር ያጐደለ፣
ይቈጠራል ሰውን እንደገደለ፤
ስለምን ይህ ሆነ ከተባለ፣
በእርሱ የአምላክ ፍቅር ስለሌለ፣
ሰይጣናዊ ስሜቱን እየተከተለ፣
ሌላውን በክፋት እየወነጀለ፣
ሰውን ሁሉ በውሸት እያታለለ፣
ከፈጣሪውም ርቆ ከሰይጣን እየኮበለለ፣
በሃይማኖቱም ምንም ስላልበሰለ፣
በጸጋም በጭራሽ ስላልተጠለለ፣
ጥላቻን ብቻ እየፈነቃቀለ፣
ሰውን ሁሉ እየከፋፈለ፣
የዋሆችን በፈተና ውስጥ ስለጣለ፣
በኃጢአት ገዳይ ነው ተባለ።


ሰው በጥላቻ ውስጥ ከተዘፈቀ፣
በኃጢአቱ አጕል እየተመጻደቀ፣
ከእግዚአብሔር ከቶ ራቀ፤
በጸጋም ካምላክ ፈጽሞ ስላልተመረቀ፣
በክፋት ብቻ እየቦረቀ፣
ያልወደደውን ሁሉ እየናቀ፣
ሓቅን ከውሸት እየደባለቀ፣
የሚስማማውን ብቻ እያደነቀ፣
እርሱ ያለው ሁሉ ካልጸደቀ፣
ልቡ በንዴት እየሞቀ፣
እየመሰለው ሐሳቡ የተሰረቀ፣
የጠላውን በአንደበቱ እያደቀቀ፣
አይቀበልም አንድ ሰው ከርሱ ከላቀ።


ሰው አንዴ በጥላቻ ከከፋ፣
ይሆናል የዲያብሎስ አካፋ፣
እየጠራረገ ሁሉን  የሚያጠፋ፣
በሕይወቱ ስለሌለው ምንም ተስፋ፣
ሰውን ወደ ጥፋት ብቻ እየገፋ፣
የኵነኔንም መንገድ እያስፋፋ፣
በክፋት ላይ ክፋትን እየጨመረ በይፋ፣
በፍጹም አይቀበልም ከሰው ነቀፋ፣
ትሕትናን ትቶ በትዕቢት እየተነፋ፣
ሥራው ከንቱ ነው ምንም ቢለፋ።


ጥላቻ ከበዛ፣
ኅሊና ይሆናል ደንዛዛ፣
ፍቅር ደግሞ ቀዝቃዛ፣
አእምሮም ፈዛዛ፣
ሃይማኖት ዋዛ፣
ስለሚጐድለው የአምላክ እገዛ፣
ይቀራል ለሰይጣን እንደተገዛ፣
ደርሶበት የአምላክ ውገዛ፣
አይነሳም ከቶ ከተገነዛ፣
ስላልነበረው የፍቅር መዓዛ።


ጥላቻ እውነትን ከውሸት እያማታ፣
ችግርን ከመፍታት ፈንታ፣
ወገንን ከወገን እየገታ፣
እያራቀ ሰውን ከፈጣሪው ጌታ፣
ጨርሶ ለሰው አይሰጥም ፋታ፣
አይታወቀውምና ሰላምና ደስታ፣
ጨርሶ ስለማይሻ የኃጢአትን ይቅርታ፣
ስለሚጐድለውም የጸጋ ስጦታ፣
የጠላውን ሁሉ ሊያንገላታ፣
ዕረፍት የለውም ጥዋት ከማታ፣
ህውከትን ለመፍጠር በሁሉም ቦታ።


ጥላቻ ለኅብረተሰብ አደገኛ መርዝ፣
የሚያስፈነክት በጠርሙዝ፣
ደምን የሚያስፈስስ እንደ ወንዝ፣
አአምሮን የሚያደበዝዝ እንደ ብርዝ፣
እያስመሰለ ገዳይን እንደ ጐበዝ፣
የማይፈራ የአግዚአብሔርን ትእዛዝ፣
እህልን እንደሚያጠፋ ጐጂ ነቀዝ፣
ሰውን እየለወጠው ወደ መጥፎ ግብዝ፣
በጽድቅ ፈንታ በክፋት የሚቅበዘበዝ፣
ያሳጣል ከፈጣሪ መንፈሳዊን ደሞዝ፣
ሰውን አስሮ የሚያስቀር በኵነኔ መግነዝ፣
እስከ ዕለተ ሞቱ በፈጣሪ ላይ ስለሚያፌዝ።


ጥላቻ ጕዳት እንጂ ጥቅም የለውም፣
እያለያየ ወንድምን ከወንድም፣
ፍቅርንና ሰላምን በማውደም፣
ወገን ከወገን በማቀያየም፣
እያጠፋ የሌላውንም ጥሩ ስም፣
ከሀገር ጨርሶ አንዲጠፋ ሰላም፣
ለዲያብሎስ እንዲገዛ ዓለም፣
ሰውም እንዲገባ ወደ ገሃነም፣
በአምላክ ተፈርዶበት ለዘላለም፣
ከቶ ሳይተው የገባውንም በገዳም፣
ሁሉን ያስታል እጅግ በጣም።


ከጥላቻ የተነሳ፣
ፈጣሪ እየተረሳ፣
በዛ የሰው አበሳ፣
እየሆነ ውሸታም አንካሳ፣
ከወደቀበት የማይነሳ፣
የማይፈጽም የኃጢአቱን ካሳ፣
ይኖራል ላገሩ ሰላምን እየነሳ፣
ልክ እንደ መከነ ማሳ፣
በክፋት ብቻ የከሳ፣
እየተሰቃየ በኅሊና ወቀሳ፣
ኃጢአቱን ሁሉ ስለማይረሳ።


በጥላቻ ውስጥ የተዘፈቀ ሰው፣
በቍመናው እንደተኰነነ ነው፤
ሌት ተቀን ይህ ሰው የሚቃጠለው፣
ሁላንችን በየቀኑ እንደምናየው፣
በንዴትና በቂም ቃጠሎ ነው፤
እውስጡ ፍቅርና ሰላም ስለሌለው፣
ሕይወቱ በሙሉ ብስጭትና ኀዘን ነው፤
ጥላቻ ከእግዚአብሔር ስለሚያርቀው፣
የእርሱ ጸጋም ስለ ጐደለው፣
እውስጡ ጭራሽኑ ባዶ ነው፤
በነፍሱ ውስጥ እስረኛ ሆኖ የቀረው፣
በኃጢአቱ ባምላክ ፊት መፀፀት ስላቃተው፣
ጥላቻ አእምሮውን ስላሳወረው፣
በቂምና በቀል ስሜት በገነባው፣
እስርቤት ነው የገባው፣
ስላጣ ከዚያ የሚያወጣው፣
ለሰይጣን ምርኮኛ ነው የሚሆነው፣
ይኸ የሆነው
ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን ስለመረጠ ነው።


 በጥላቻ የተማረከ ሰው፣
በጣም ደካማ የሆነው፣
የአምላክ ፍቅር ስለሚጐድለው፣
እንደ ከበሮም የሚጮኸው፣
እውስጡ በጭራሽ ባዶ ስለሆነ ነው፣
የራሱ  ጐደሎነት ስለማይታየው፣
የሌሎችን ብቻ ነው የሚመለከተው፣
ሌሎችንም በጅምላ የሚጠላው፣
ፈጽሞ እራሱን ስለማያውቅ ነው፤
ሌላን የሚጠቅም እየመሰለው፣
እራሱን ነው የሚጐዳው፤
እንደዚህ ከመሰለው ሰው፤
እግዜር ብቻ ያድነን ነው፣
ስለምን በጥላቻ የታወረው፣
የሚመራው ወደ ጕድጓድ ብቻ ነው።


በጥላቻ ሰው ለሌላ ክፋትን እያወረሰ፣
የጠላውን በፖለቲካ ስም እየከሰሰ፣
መልካም ሥራውንም በጥላቻ እየደመሰሰ፣
ጻድቁንም ሳይቀር በመጥፎ ስም እያረከሰ፣
የጠላቸውን ሁሉ የኀጢአት ካባን እያለበሰ፣
ከክፋትና አበሳ በፍጹም ስላልታገሰ፣
ወገን ሁሉ ተቸገረ የሰላም እጦት እየተባባሰ፤
ስለምን የአምላክ የፍቅር ትእዛዝ እንዳለ ስለተጣሰ።


ሰው ሰውን በጥላቻ የሚፈርጀው፣
እውስጡ ተመልቶ ካለው፣
የጥላቻ መንፈስ ነው፤
ወደ ሌላ የሚያንጸባርቀው፣
እውስጡ ከተሞላው፣
አንጀቱን ከሚያሳርረው፣
ዕረፍትን ከሚያሳጣው፣
የአእምሮ ሰላምን ከሚነሳው፣
ብስጭትና ንዴት የወጣ ነው፤
ይህ የሚያመለክተው፣
የእግዜር ጸጋ እንደጐደለው፣
እራስንም የመቈጣጠር ኃይል እንደሌለው፣
ማንንም መጥቀም እንደማይችል ነው፤
ይህ ነገር በውኑ ከተረዳነው፣
ታዲያ ወገኖቼ ለምንድር ነው፣
ይኸን ዓይነት ሰውን የምንከተለው፣
ምንስ ፋይዳ ቢኖረው ነው?


ጥላቻ ሰይጣንን ያስደስታል፣
እግዚአብሔርን ግን ያሳዝናል፣
በሰው ልብ እምነትን ያቀዘቅዛል፣
ሃይማኖትን ያራክሳል ያዋርዳል፣
አእምሮን ያደበዝዛል፣
ከፈጣሪ ሰውን ያርቃል፣
ወደ ሰይጣን ያስጠጋል፣
ወደ ገሃነመ እሳት ይመራል፣
መንግሥተ ሰማይን ያስዘጋል፣
ፍቅርን ከሰው ያጠፋል፣
ሰውን ከሰው ያጋጫል፣
በሀገር ሰላምን ያደፈርሳል፣
የእርስ-በርስ ደምን ያፋስሳል፣
በማይረባ አላማ ሰውን ያስጨርሳል፣
ወገንን በጣም ይጐዳል፣
ሀገርንና ሕዝብን ይከፋፍላል፣
ለዲያብሎስ መንገድን ያመቻቻል፣
ሰው ወደ ገሃነመ እሳት እንዲጣል፣
መንገዱን ጥሩ አድርጎ ይጠርግለታል።

 

Advertisements

%d bloggers like this: