Advertisements
IRROB.ORG

Home » አስተያየቶች » ጠቃሚ ምክሮች ለወገኖች

ጠቃሚ ምክሮች ለወገኖች

የአባ ተስፋማርያም ባራኪ አስተያየቶች

ጠቃሚ ምክሮች ለኢትዮጵያውያን ወገኖች

ኢትዮጵያ የምትፈልገው፣
ሰላምን ነው፤
ሀገር የሚበለጽገው፣
በልማት ነው፤
ልማት የሚመጣው፣
ጦርነት ከጠፋ ነው፤
ጦርነት የሚጠፋው፣
ጥላቻ ሲቀር ነው፤
ጥላቻ የሚቀረው፣
የተጣሉት ሲታረቁ ነው፤
መታረቅ የሚመጣው፣
መነጋገር ሲቻል ነው፤
መነጋገር የሚቻለው፣
ትዕቢት ሲቀር ነው፤
ትዕቢት የሚቀረው፣
ትሕትና ሲኖር ነው፤
ትሕትና የሚገኘው፣
ምንነት ሲታወቅ ነው፤
ምንነት የሚታወቀው፣
ፍጡር መሆንህን ሲታመን ነው፤
ፍጡር መሆንን የሚታወቀው፣
ፈጣሪ መኖሩን በማመን ነው፤
እምነት የሚኖረው፣
ጸጋውን ካገኙ ብቻ ነው፤
ጸጋው የሚገኘው፣
በጸሎት ስለምኑት ነው፤
ጸሎት የሚደረገው፣
በንጹሕ ልብ ነው፤
ንጹሕ ልብ የሚኖረው፣
ከክፋት ከራቁ ብቻ ነው፤
ከክፋት የሚራቀው፣
ፈሪሐ-እግዚአብሔር ሲኖር ነው፤
ፈሪሐ-እግዚአብሔር የተባለው፣
አክብሮ እግዚአብሔር ነው፤
አክብሮ እግዚአብሔር የሚታየው፣
ትእዛዛቱን በመጠበቅ ነው፤
ትእዛዛቱ የሚለው፣
እርስበርሳችሁ ተዋደዱ ተማማሩም ነው፤
መማማር የሚቻለው፣
የይቅርታ መንፈስ ሲኖር ነው፤
የይቅርታ መንፈስ የሚኖረው፣
እውነተኛ ፍቅር ሲኖር ነው፤
እውነተኛ ፍቅር የሚኖረው፣
የአምላክ ፍቅር ሲያድርብህ ነው፤
ፍቅር የሚገለጸው፣
በሰው ላይ ነው፤
ሰው የተባለው፣
ወንድና ሴት ነው፤
ወንድና ሴት የተባለው፣
በእግዜር መልክ የተፈጠረ ነው፤
በመልኩ የተፈጠረው፣
ቅዱስ ነው፤
ቅዱስ የሆነው፣
የቅዱሱ አምላክ ልጅ ስለሆነ ነው፤
ቅድስና የሚጠፋው፣
ኃጢአት ሲሠራ ነው፤
ኃጢአት የሚሠራው፣
የእግዜር ጸጋ ሲጐድል ነው፤
የእግዜር ጸጋ የሚጐድለው፣
እግዜር ሲራቅ ነው፤
ከእግዜር የሚራቀው፣
ተንኰልና ክፋት ሲፈጸም ነው፤
ተንኰልና ክፋት የሚፈጸመው፣
ሰው በሰይጣን ሲፈተን ነው፤
ሰው በሰይጣን የሚፈተነው፣
በዓለም ነገር ብቻ ሲያተኵር ነው፤
በዓለም ነገር ብቻ የሚተኰረው፣
መንፈስ ሲቀዘቅዝ ነው፤
መንፈስ የሚቀዘቅዘው፣
ሰው በፍትወተ ሥጋ ሲመራ ነው፤
በፍትወተ ሥጋ የሚመራው፣
በሰይጣን ፈተና ሲማረክ ነው፤
ሰይጣን የተባለው፣
ፈታኝ ስለ ሆነ ነው፤
ሰይጣን ፈታኝ የተባለው፣
በትዕቢት ስለ ተፈተነ ነው፤
በትዕቢት የተፈተነው፣
እንደ ፈጣሪ ካልሆንኩኝ ብሎ ነው፤
እንደ ፈጣሪ እሆናለሁ ያለው፣
ፍጡር መሆኑን ስለዘነጋ ነው፤
ፍጡር መሆኑን የዘነጋው፣
ትዕቢት አድሮበት ጸጋ ስለ ጐደለው ነው፤
ጸጋ የጐደለው፣
ከፈጣሪው ስለራቀ ነው፤
ከፈጣሪው የራቀው፣
ከርሱ ጋራ ስለተጣላ ነው፤
ርሱ ጋራ የጣላው፣
ከፈጣሪ ጋራ እኩል ካልሆንሁ ብሎ ነው፤
ከፈጣሪው እኩል ያልሆነው፣
ፍጡር ስለ ነበረ ነው።
ስለዚህ አንድ ሰው፣
ካልተገዛ ለፈጣሪው፣
ልክ እንደ ሰይጣን ነው፥
እንደ ሰይጣን የሚሆነው፣
ከአምላኩ ሲርቅ ነው፥
ከአምላኩ የሚርቀው፣
ሰይጣንን ሲከተል ነው፤
ሰይጣንን የሚከተለው፣
በፈተናው ተሸንፎ ነው፤
በፈተናው የሚሸነፈው፣
የሰይጣንን ምክር ስለሚቀበል ነው።
እስቲ እንስማው፣
ሰይጣን ክርስቶስን ሲፈትነው፣
በትዕቢት ተነሳስቶ ያለው፤
የእግዜር ልጅ ከሆንህ እንደሚባለው፣
ድንጊያውን ወደ ዳቦ ለውጠህ ብላው፤
ነበር ያለው በጾም ደክሞ ስላየው፤
በንቀት ነበር የተመለከተው፤
እንደ ደካማም የቆጠረው፤
ረዳት እንደሌለውም ያየው፤
ክርስቶስ ፈተናውን ሲያሸንፈው፣
አልበቃ ብሎት ወደ ተራራ አወጣው፤
ዓለምንም በሰፊ አሳየው፤
ያ ሁሉ ግዛቴ ነው፤
ወድቀህ ብትሰግድልኝ ላንተ ነው፣
እያለ ተናገረው፤
ኢየሱስ ግን ተከራከረው፤
በመጽሐፍ የተጻፈው፣
ላንድ ፈጣሪ አምላክ ብቻ ስገድ ነው፣
እያለ ከፊቱ አባረረው።
እስቲ በእውነቱ ስናስበው፣
ከዚሁ ምሳሌ የምናገኘው፣
ምን ዓይነት ትምህርት ነው?
ክርስቶስ እንዳለው፣
ሰይጣን በጣም አደጋኛ ነው፤
ሰምቶት ለተከተለው፣
በፈተናውም ለተማረከው፣
በትዕቢቱም ለተመራው፣
ምክሩንም ለተቀበለው፣
ማጥፋቱ ነው ሥራው።
ሰይጣን የሚመራው፣
ወደ ገሃነመ እሳት ነው፤
ሥራውን የሚሠራው፣
በሰው አማካይነት ነው፤
ሰውን የሚቆጣጠረው፣
በትዕቢት መንፈስ ነው፤
ሰውን እስረኛ የሚያደርገው፣
በኃጢአት ነው፤
ኃጢአት የሚያመጣው፣
የነፍስን ጉዳት ነው፤
የነፍስ ጉዳት የሚያስከትለው፣
የነፍስን ሞት ነው፤
የነፍስ ሞት የተባለው፣
ዘለዓለማዊ ኵነኔ ነው፤
ይህ ሁሉ የሚመጣው፣
ሰይጣንን በመከተል ነው።
ስለዚህ እንደተባለው፣
ሰይጣን የጥፋት መንፈስ ነው፤
በሥራው እንደሚታወቀው፣
ሁሉን ማተራመስ ነው፤
ሁሉን የሚያተራምሰው፣
የጥላቻን መርዝ በመንዛት ነው፤
መርዙን የሚነዛው፣
በፖለቲካ በጎሳነት በዘርነት ነው፤
ፖለቲካ የሚያመጣው፣
የሓሳብ ልዩነትን ነው፤
የሓሳብ ልዩነት የሚያመጣው፣
የሐሳብ ግጭትን ነው፤
የሐሳብ ግጭት የሚወልደው፣
መለያየትን ነው፤
መለያየት የሚፈጥረው፣
አለመስማማትን ነው፤
አለመስማማት የሚመራው፣
ወደ መቀያየም ነው፤
መቀያየም የሚያስከትለው፣
መኰራረፍን ነው፤
መኰራረፍ የሚወስደው
ወደ ቂምና በቀል ነው፤
ቂምና በቀል የሚያስከትለው፣
የደም መፋሰስን ነው፤
ደም መፋሰስ የሚያመጣው፣
እርስ-በርስ መፋጀትን ነው፤
ይህ ሁሉ የሚታወቀው፣
እንደ ሰይጣን ሥራ ነው፡፡
ስለዚህ ፈጣሪ የሚለው፣
ልጄ ሆይ ኤረ ተው!
ሰይጣንን አትከተለው!
ፈተናውን አትቀበለው፤
የፍቅር ጥሬን አድምጠው፤
ትእዛዛቴን ጠብቀው፤
ትእዛዛቴ የሚለው፣
ሰውን ሁሉ እኵል ውደደው፤
የበደለህን ይቅር በለው፤
የተበደልከውን ለኔ ተወው፤
ስለምን ፈጣሪው ፈራጅው፣
ሁለቱም እኔ እራሴው።
ምን ነበር ሐዋርያው ያዕቆብ የጻፈው?
እስኪ ልብ አድርገን እናንብበው፤
መልእክቱ የሚናገረው፣
ስለ ዓለም ክፋት ነው፣
“በእናንተ መካከል ያለው፡
ጦርነትና ጠብ የመጣው፣
በልባችሁ ውስጥ ካለው፣
ከሥጋዊ ምኞታችሁ ነው”።
ሐዋርያው እንደሚለው፣
ሰው ሰውን የሚጠላው፣
ሰው ሰውን የሚገድለው፣
የፈለገውን ነገር ማግኘት ሲያቅተው፤
ሰው ከሰው የሚጣላው፣
የተመኘውን ማግኘት ሲያቅተው፤
ሰው የፈለገውን የማያገኘው፣
ስለማይጸልይ ነው፤
ሲጸልይም ጸሎቱ የማይሰማው፣
መልሱንም የማያገኘው፣
በክፉ አሳብ ሲጸልይ ነው፤
አሳቡ የሚያተኵረው፣
በሥጋዊ ደስታ ላይ ሲሆን ነው፤
ሥጋ የሚፈልገው፣
የዓለምን ነገር ነው፤
ሐዋርያው ግን ያለው፣
በሥጋዊ ምኞት የተገዛው፣
በዓለም ፍቅርም የተማረከው፣
የእግዚአብሔር ጠላት ነው የሚሆነው።
መጽሐፉ ግን የሚለው፣
አምላክ መንፈሱን በልባችሁ ያሳደረው፣
ለእርሱ ብቻ እንድትገዙ ነው፤
ይህም የሆነው፣
እርሱ ከልቡ የሚመኘው፣
ደኅንነታችሁን ስለሆነ ነው።
ግን ሐዋርያው እንድሚያስረዳው፣
ያ ዲያብሎስ የተባለው፣
የእግዚአብሔር ጠላት የሆነው፣
በጣም አደገኛ ነው፤
ፍቅር ስለሌለው፣
በጥላቻ መንፈስ ነው
ሰውን የሚመርዘው፤
ደስታ የሚባል ስለሌለው፣
ዘወትር ኀዘንተኛ ነው፤
ሕይወቱ የሚሰቃየው፣
በማይጠፋ ዘላለማዊ እሳት ነው፤
በሰውም ላይ የሚቀናው፣
በዚሁ ምክንያት ነው፤
ሥራው ሁሉ ምቀኝነት ነው።

ስለዚህ ያዕቆብ ሐዋርያው፣
መልእክቱን ሲጽፈው፣
እንዲህ ነበር ያለው፣
እግዚአብሔር ትዕቢተኛውን ሲቃወመው፣
ለትሑቱ ግን የሚሰጠው፣
የበለጠውን ነው።
እንግዲያውስ ለፈጣሪህ ተገዛው፣
ዲያብሎስን ግን ተቃወመው፣
ካንተም እንዲሸሽ አድርገው፤
ለእግዚአብሔር ግን ቅረበው፣
ልብህንም ስጠው።
ነፍስህን በንስሐ አጽዳው፣
ክፋትንና ተንኰልን ተው፤
ያኔ ነው አምላክ ወዳንተ የሚጠጋው፤
በፊቱ ራስህን ዝቅ ስታደርገው፣
ያኔ ነው ልብህን በደስታ የሚሞላው፤
ከሁሉም ጋራም በሰላም የምትኖረው፣
ወገኖችህንም የምትጠቅመው፣
አገርህንም የምታበለጽገው፤
ሰይጣንን ከድተኸው፣
የእግዚአብሔር ልጅ ስትሆን ብቻ ነው።

 

 

 

Advertisements

%d bloggers like this: