Advertisements
IRROB.ORG

Home » አስተያየቶች » እግዚአብሔር ወይስ ሀገር?

እግዚአብሔር ወይስ ሀገር?

የአባ ተስፋማርያም ባራኪ አስተያየቶች

የፈጠረ ወይስ የተፈጠረ?

ኤረ ለመሆኑ ማን ነው እግዚአብሔር፣
ሀገርስ ምንድርነው ከእግዚአብሔር አንጻር፣
ረጋ ብለን ከልብ ብንመረምር፣
አእምሮን ነው የሚያሸብር፤
ሰው የሚያሳየው ሀገራዊ ፍቅር፣
ለፈጣሪ ብቻ የሚገባ ክብር፣
ሰው ሲሰጥ ይታያል ለምድራዊ ሀገር።
ስለ አምላክ ፈጣሪ ግን መናገር፣
ለሰው ልጅ እጅግ በጣም ጥልቅ ምሥጢር፣
ለመግለጹና ለመረዳቱ አእምሮን የሚያደናግር፣
ሆኖም ግን ከቶ አይቻልም ያለሱ መኖር፤
ስለምን እግዚአብሔር ነው ሁሉን በመፍጠር፣
በእውቀቱና ችሎታው ዓለምን የሚያስተዳድር፣
ከፍጡራኑም ጋራ በጣም ደግና ቼር፣
ጻድቃንንና ኃጥአንን እኩል ጠብቆ የሚያሳድር።
ሰው ግን እራሱን እያስገባ ከማይወጣበት ችግር፣
ስለ ችግሩም በፈጣሪ ላይ በማማረር፣
ይታያል ከሰይጣን ጋራ ሲያብር፤
የፈጣሪውን ሕግ አጥብቆ ከማክበር፣
በትዕቢት የራሱን ሕግ በመፍጠር፣
የአምላክን ሕግ ችላ ብሎ በመሻር፣
ሲገባ ይገኛል ከማያዋጣው ውዥንብር።
መሬትም እየተቈረሰች በየቍራጭ ሀገር፣
እየገባችም በፍጡር ሥልጣን ሥር፣
ሰው ይረበሻል አብሮ በሰላም እንዳይኖር፤
አንድ መንግሥስት ሌላን በመውረር፣
አንድ ሕዝብም በሌላው ላይ ቦምብ በመወርወር፣
ደም ይፈሳል ሰው እርስበርስ እንዲቃቃር፤
ጭካኔና ጥላቻ ይነሳል ሰው እንዳይማማር፣
ይኸ ሁሉ ለሥልጣን ፍቅርና ውድድር።
ያልቻለ የጥላቻውን ስሜት መቈጣጠር፣
ሲሯሯጥ ይታያል ሀገርን ለማስተዳደር፣
እየመሰለው ያለው የወገን ፍቅር፤
ግን ሰው ተመሊሶ ወደ እግዚአብሔር፣
እውነቱን ከልቡ አውጥቶ ቢናገር፣
የራሱንም ሕይወት ከልቡ ቢመረምር፣
ኃጢአቱንም ሁሉ በደምብ ቢቈጥር፣
እራሱንና ሌላውን በከንቱ ባላወናበደ ነበር፤
ስለሚታየው የግሉ ደካማው ስነምግባር።
አንድ ቤት ስለማይታነጽ በአየር፣
የሚመካ ሁሉ ለወገንና ሀገር፣
መጀመሪያ ይገዛ ለእግዚአብሔር፤
ሰው ሁሉ በሰላም እንዲተዳደር፣
እንዲኖርም በፍቅርና መከባበር።
ዋጋ የለውም በአፍ ብቻ መፎከር፣
እያስመሰለ የሆነ የሰው ሁሉ ገር፣
እውስጡ እያለ ነጣቂ ነብር፣
ሰውን ሁሉ የሚያስሸብር፣
ያልተቈጠበና ያልጸዳ ከክፉ ምግባር፣
እንደ ነብር ቆዳ ዝንጕርጕር።
ኤረ ለመሆኑ ስለ ሀገር ስንናገር፣
ይበልጣል ወይ ሀገር ከእግዚአብሔር፣
ያ ሁሉ ለሀገር የሚሰጠው ፍቅርና ክብር፣
ይገባ አልነበረም ወይ ለፈጣሪ ኄር?
ከአምላክ ይልቅ ሀገርን ማክበር፣
የተሳሳተ የፖለቲካ ተግባር።
ሰው እንዳይኖር በመንፈሳዊ ሥነ ምግባር፣
ተፋቅሮ እንዳይኖርም በአምላክ ሕግ ሥር፣
በሀገራዊ ስሜት ብቻ በመታወር፣
ይታያል በየቦታው ሲከት የዘመቻን ጦር፤
ሰው ከሰው አብሮ በሰላም እንዳይኖር፣
አንዱ በሌላው ላይ በዛቻ በሞፈከር፣
አንድ ወገን ከሌላ ጋራ እንዳይተባበር፣
መለያየትን በሰው መካከል በመፍጠር፣
እንደ በሬ ተጠምዶ በፖለቲካ ሞፈር፣
ሲገባ ይታያል ከማይወጣበት ቀንበር፣
እየዘነጋ ከሞት በኋላ የሚጠብቀውን መቃብር፣
እየመሰለውም በዚህ ምድር ለዘላለም የሚኖር።


የዛሬው ኢትዮጵያውያን ሴቱ ወንዱ
ሀገርን ከፈጣሪ በላይ እየወደዱ፣
በሕዝባቸውም ላይ በፖለቲካ እየነገዱ፣
በጐሳነትና ዘረኝነት-ጥላቻ ብቻ አበዱ፤
በቍጣና በበቀል ስሜት እየነደዱ፣
ጠላትንም ሳይቀር እንደራስ ውደዱ፣
የሚለውን የአምላክ ትእዛዛትን ካዱ፤
የጠሉትን ብቻ እንዳለ እንዲጐዱ፣
ከዲያብሎስም ጋራ እየተዛመዱ፣
በቀልን ይመርጣሉ ወደ ገሃነም ኣስኪወርዱ፣
ለዘለዓለምም በስቃይ ኵነኔ እንዲዋረዱ።

Advertisements

%d bloggers like this: