Advertisements
IRROB.ORG

Home » አስተያየቶች » ስለ ፍቅር

ስለ ፍቅር

የአባ ተስፋማርያም ባራኪ አስተያየቶች

ስለ ፍቅር

ፍቅር የተባለው ነገር፣
ሁሉን በአንድነት የሚያስር፣
የሚመነጨውም ከእግዚአብሔር፣
ሰውን በመልኩ የሚፈጥር፣
ለዘላለም በደስታው እንዲኖር፣
ተለውጦ ወደ ደግና ቼር፣
እንዲገባም በገነት በር፣
ከመላእክት ጋራ እንዲዘምር፣
ከፈጣሪው ጋራም ተደስቶ ለመኖር፣
ስለምን እራሱ ነውና እውነተኛው ፍቅር።


ፍቅር በጣም ነው ኃያል

ፍቅር በጣም ነው ኃያል፣
ስለምን ከእግዚአብሔር ይመነጫል፤
ብዙ ጸጋን ያወርዳል፣
ሰላምን ለሰው ያመጣል፣
አንድነትን ይፈጥራል፣
እውነተኛ ደስታን ይሰጣል፣
ከሰው ጥላቻን ያጠፋል፣
በጥላቻ የታመሙትን ይፈውሳል፣
በመንፈስ የደከመውን ያበረታታል፣
የተጣሉቱን ያስታርቃል፣
በደልን ሁሉ ይቅር ይላል፣
ቂምና በቀልን ይረሳል፣
ለበደሉትም ምሕረትን ያደርጋል፣
ከኵነኔም ሰውን ያድናል፣
ወደ ደኅንነትም ያደርሳል።


ፍቅር ነው ችግርን የሚፈታ

ፍቅር ነው ችግርን የሚፈታ፣
የሚፈውስም ከጥላቻ በሽታ፤
ሰው እንዲኖር በሰላምና ደስታ፣
ጥል ጠፍቶ እንዲነግሥ ጸጥታ፣
ስምምነትም እንዲስፋፋ በሁሉም ቦታ፤
ጠብ ሲነሳም አንድም ሳይማታ፣
ቍጭ ብሎ በመነጋገር በአንድ ገበታ፣
መፍትሔን የሚያስገኝ ለሁሉም ዉካታ፤
ይመራል ወደ እውነተኛው ይቅርታ፣
ያ ትልቁ የእግዚአብሔር ሥጦታ፣
ምሕረትን የሚሰጥ በበቀል ፈንታ፣
ፍቅር በውነቱ ትልቅ የመንፈስ ርካታ፣
ሰውን በጣም የሚያበረታታ፣
ጥላቻንና ክፋትን ሁሉ እየገታ፣
ሰውን የሚመራ ወደ ፈጣሪው ጌታ፣
እየጠበቀው ከጥዋት እስከ ማታ፣
እንዳይሸነፍ በሰይጣኑ ወስላታ።


ፍቅር ካለ

ፍቅር ካለ፣
በጥላቻ የቈሰለ፣
በጸጋ ተጠለለ፣
በሰላምም ዋለ፤
ያ በቍጣ የጋለ፣
በጣም ረጋ አለ፤
ደስተኛም እየመሰለ፣
ሁሉን በትዕግስት ተቀበለ፤
ሁሉንም ይቅር አለ፤
ክርስቶስን መሰለ፤
በሰይጣን ፈተና ስላተታለለ፣
ጽድቅን ብቻ እየተከተለ፣
ሁልጊዜም በዚሁ ስለቀጠለ፣
ጻድቅ ነው ተባለ፤
በእውነቱ ፍቅር ካለ፣
ሁሉ ነገር አለ።


የእግዚአብሔር ፍቅር

እስቲ ልዘምር፣
ለልዑሉ እግዚአብሔር፣
እርሱ ነውና ሁሉን በመፍጠር፣
በጥበቡ ዓለምን የሚያስተዳድር፣
ስለሆነ እራሱ እውነተኛው ፍቅር፤
ከሁሉም ጋራ በጣም ቼር፣
የሚል በድልን ይቅር፤
ሰው ከእርሱ ጋራ እንዲኖር፣
ይከፍትለታል የገነትን በር፤
ያዘጋጅለታልም የክብርን ወንበር፣
እንዲረሳ ያሳለፈውን ቀንበር፣
በትልቅ ፈተናና ችግር፣
በዓለማችን በዚህ ምድር፣
ስለሆነ እጅግ በጣም ገር፤
አይቻልም ለማንም ፍጡር፣
ከእርሱ ተለይቶ መኖር፤
እንዘምርለት በፍጹም ፍቅር፣
ለፈጣሪያችን ታላቁ ኄር፤
በጣም ድንቅ ነው የእርሱ ነገር፣
ምንም እንኳን ከዓይናችን ቢሰወር፣
ለአእምሮአችን ቢሆንም ጥልቅ ምሥጢር፣
ሥራው ድንቅ ነው በጣም መስተንክር፣
በቼርነቱ ሁሉን እኩል የሚያስተዳድር።


ፍቅር ነው ልብን የሚያረካ

ፍቅር ነው የሁሉን ልብ የሚያረካ፣
አንድንም ሰው በበደል ሳይነካ፣
ትሕትናን የሚያሳይ በኃይሉ ሳይመካ፤
ለሁሉም ጥላ እንደ ትልቅ ወርካ፣
በደግነቱና ቼርነቱ የማይለካ፣
የሚለውም ስጠኝ ሳይሆን ሁልጊዜ እንካ።


ፍቅር የሰው ልጅ ተስፋ

ፍቅር የሰው ልጅ ተስፋ፣
በሁሉም ቦታ እንዲስፋፋ፣
ሁሉም ሰው ለመፋቀር ይልፋ፤
ማንም ሰው በጥላቻ እንዳይገፋ፣
ይልቅስ እንዲያገኝ የሰላምን ወረፋ፣
ፍቅር ብቻ ይሰበክ በይፋ፣
የሰው ልጅ እንዳይጠፋ፣
በጥላቻና ክፋት እየከረፋ።


ፍቅር ብርቱ ነው

ፍቅር በጣም ነው ጠንካራ፣
ለሰው ሁሉ እኩል የሚራራ፣
ከእግዚአብሔር ጋራም ስለሚጋራ፣
ምንም የለውም ባለጋራ፤
በትእዛዛቱም ለሚመራ፣
ሞትን እንኳን አይፈራ፤
ይበራል እንደ አሞራ፣
ወደ ሰማዩ ተራራ፣
ሳይነካው የጥላቻው አቧራ።


ፍቅር ከነገሠ

ፍቅር ከነገሠ፣
የሰይጣን ግዛት ፈረሰ፤
ጥላቻም ተደመሰሰ፤
በዚህም አምላክ ተሞገሰ፣
ሰይጣን ግን ተከሰሰ፤
ጸጋም ከሰማይ ፈሰሰ፤
ሰውም ሰላምን ለበሰ፤
ደስታንም ወረሰ፣
የጽድቅን ፍሬ እያፈሰ።


ፍቅር ካለበት ቦታ

ፍቅር ካለበት ቦታ፣
የሰው ልጅ እንዳይንገላታ፣
አለበት እራሱ ፈጣሪ ጌታ፣
ሰው እንዲኖር በሰላምና ደስታ፣
እንዲገኝም የመንፈስ ርካታ፣
እንዲጠፋም የጦርነት ዉካታ፣
ጥላቻን ሁሉ እየገታ፣
ያስቀራል የቦምብን ፍንዳታ፤
እንዲነግሥም ፍጹም ጸጥታ፣
ማንም ሰው በጥል ሳይማታ፤
ነገር ሁሉ በሰላም ብቻ እንዲፈታ፤
ይኸ ሁሉ የእግዜር ውለታ!
ደግነቱ በጣም ነውና በርካታ፣
ምስጋና ይድረሰው ቀንና ማታ!


ፍቅር ሰውን ይለውጣል

በጥላቻ የነበረው በሽተኛ፣
በፍቅር ይሆናል ጤነኛ፤
በጥላቻ የነበረው ብቸኛ፣
በፍቅር ያገኛል ጓደኛ፤
በጥላቻ የነበረው ጥለኛ፣
በፍቅር ይጋራል ላዛኛ፤
በጥላቻ የነበረው ቍስለኛ፣
በፍቅር የሆናል የፍትሕ ዳኛ፤
በጥላቻ የነበረው ውሸተኛ፣
በፍቅር ይሆናል እውነተኛ፤
በጥላቻ የነበረው እልኸኛ፣
በፍቅር ይተባበራል ሳይተኛ፤
በጥላቻ የነበረው አበሰኛ፣
በፍቅር ይሆናል የወገን መተማመኛ፤
በጥላቻ የነበረው ከዳተኛ፣
በፍቅር ይሆናል የሰላም አርበኛ።


ፍቅር ከጠፋ

ፍቅር ከጠፋ፣
ሰው የለውም ተስፋ፤
ምንም እንኳ ቢለፋ፣
ነገር ሁሉ እንደ ከፋ፤
ውሸት ብቻ እየተውራ በይፋ፣
ክፋትና ተንኰል እየተስፋፋ፣
የሰው ስምም እየጠፋ፣
መብቱም ሁሉ እየተገፋ፣
ሰው ይማታል በአካፋ፤
በፍጹም ይታጣል የሰላም ወረፋ፤
ከትግራይ ጀምሮ እስከ ካፋ፣
ኢትዮጵያዊው ሁሉ ለፍቅርና ሰላም ካልለፋ።


የሰው ልጅ ከተፋቀረ

የሰው ልጅ ከተፋቀረ፣
ጥላቻ ሁሉ እየቀረ፣
የሰው ልጅ በሰላም ኖረ፤
በደልን ሁሉ እየማረ፣
ሕይወቱ በአምላክ ጸጋ ስላማረ፣
ጽድቅ በጽድቅ ላይ እየጨመረ፣
በበጐነት ሥራ እየተወዳደረ፣
ሐሳቡ ወደ ሰማይ እየተወረወረ፣
የፈጣሪውን ሕግ እያከበረ፣
ለተቸገረው ሁሉ እያበደረ፣
በስግብግብነት ስላልተቀረቀረ፣
በመልካም ሥራው እየፎከረ፣
እንዳሞራ ወደ ሰማይ በረረ፤
ልቡ ረክቶ ተደስቶ አደረ፤
ከአምላኩና ከሰው ሁሉ ስለተፋቀረ፣
በእግዚአብሔርም ዘንድ ከበረ።


ፍቅር የሰላም ከተማ

ፍቅር የሰላም ከተማ፣
በእግዜር ጸጋ የሚለማ፤
ሰው ቃለ ወንጌልን እየሰማ፣
በሁሉም ነገር ስለሚስማማ፣
በጥላቻ ሌላን ሳያማ፣
ይረዳል የሆነውን ደካማ፣
እንደ ወላጅ እማማ፣
የሚታሳድግህ በጀርቧ ተሸክማ፤
ሌት ተቀን በጣም ደክማ፤
መሥዋዕትነት ለርሷ ታላቅ ግርማ፣
ፍቅር ብቻ ነውና የርሷ አርማ፣
ሌላውን ታስደስታለች ከራሷ አስቀድማ፤
የፍቅር ትልቁ ዓላማ፣
ሰው በብርሃን እንዲኖር ወጥቶ ከጨለማ፤
ጽድቅን እያካበተ ከፍሬያማው አውድማ፣
እንደ ጻድቁ ባሕታዊ አባ ገሪማ፣
ዓለምን የመነነ በኃጢአት እንዳይገማ፤
በእውነቱ ፍቅር ያበራል እንደ ሻማ፣
እንደ አባታችን አባ ሰላማ፣
ከሣቴ ብርሃን ለአክሱም ከተማ፣
ኢትዮጵያን በሃይማኖት ያለማ።


ፍቅር እንዲበዛ…

ፍቅር እንዲበዛ፣
ይስፈልጋል የአምላክ እገዛ፤
ሁሉም ለትእዛዛቱ ከተገዛ፣
ኅብረተ ሰብ ይኖሯል መዓዛ፤
ሃይማኖትም አይታይም እንደ ዋዛ፤
ሰላም ይሆናል ከአሜሪካ እስከ ጋዛ፤
ከቶ አይገኝምምና ተገድሎ የተገነዛ፣
በፍቅር ስለተለወጠ እንደ ቅድስት ተሬዛ፣
በቅድስና የዳበረች ጸጋዋ ሁሌ እየበዛ።


ሰው በፍቅር ካልተረዳዳ

ሰው በፍቅር ካልተረዳዳ፣
ብዙ ሰው ስለሚጐዳ፣
ሰው አይሁን ለእያንዳንዱ እንግዳ፣
ሁሉ ሰው ሁሉን ይርዳ፤
አሊያ ይሆናል የሰው ወራዳ፣
ወዳጅ እንደሌለው ቡዳ፤
ብቻውን የሚኖር እምድረቤዳ፤
በጸሐይ ቃጠሎ እንዳረረ ጽጌረዳ፣
ተሰብሮ እንደማይነሳም አገዳ።


ፍቅር ነው ለሁሉ ነገር የሚበጅ

ፍቅር ነው ለሁሉ የሚበጅ፣
የሚያደርግህ የአምላክ ልጅ፣
እርስበርስም እንድትሆን ወዳጅ፣
ያስቀራል ከመሆን በሌላ ላይ ፈራጅ፣
ከማፍሰስም በሌላ ላይ የጥላቻን ነዳጅ፣
እንድትገባ ዘንድ በዲያብሎስ እጅ፣
የጠላኸውን እንድትጐዳ በክፋት ፈንጅ።


ሰው እግዚአብሔርን ካፈቀረ

ሰው እግዚአብሔርን ካፈቀረ፣
መንፈስ ቅዱስ በርሱ ውስጥ ስላደረ፣
በደልን ይቅር ማለትን ተማረ፤
ሆዱም በንዴትና ጥላቻ ስላላረረ፣
በሰላምና ደስታ መኖርን ጀመረ፤
መለኮታዊውንና ሰብአዊውን እያቀነባበረ፣
ለቅዱስ ሥራ ከመላእክት ጋራ ተወዳደረ፤
እንደ አሞራ መንፈሱ ወደ ሰማይ እየበረረ፣
ሕይወቱና ዝናው በጣም አማረ፣
በሕዝብም ዘንድ እጅግ በጣም ተከበረ፣
በስሙም መዝሙር ተዘመረ፣
ከውዳሴውም የለም ማንም የቀረ።


ፍቅር ባለበት

ፍቅር ባለበት፣
ይቻላል መግባባት፣
መድረስ ወደ አንድነት፣
እርስበርስም መረዳዳት፣
መኖር በሙሉ  ነፃነት፣
እንደ ሕዝቡ ምኞት፣
ሳይኖር በሀገር ጦርነት፣
በሃይማኖቶችም ልዩነት፣
ልብ ነጥቶ ከክፋት፣
ንስሐ ተገብቶ ከኃጢአት፣
ተቀድሶ እንደ መላእክት፣
ከሚኖሩት በገነት፣
ሳይቃጠሉ በእሳት፣
ስላልተነኩ በትዕቢት፣
እንደ እኩያኑ መናፍስት፣
የተኰነኑ ከፈጣሪ በመሸፈት፤
ፍቅር ነው ትልቅ ምቾት፣
ከሁሉ የበለጠ ሃብት፣
ከፈጣሪ የሚገኘው በረከት፣
ሰው እንዳይቸገር በሰላም እጦት፣
ፍቅር በውኑ ያመጣል ትልቅ ውጤት።

ፍቅር ነው ከጥላቻ እስርቤት የሚያወጣ፣
ታላቁ ኃይል ከእግዚአብሔር የሚመጣ፣

የሰው ልጅ በዚህ ዓለም ሰላምን እንዳያጣ፣
እንዳይገባ ከማይወጣበት ታላቁ ጣጣ፣
ፍቅር ነው ለሁሉም መድኃኒቱ የነፃነት ዕጣ፣
በጥላቻ መንፈስ እንደ ተልባ የማይንጣጣ፣
ነፍስን የማያበክል በንዴትና ቍጣ፣
ፍቅር ይረዳል ሰው ከክፋት እንዲነጣ፣
በጥላቻ ምክንያትም ለዘላለም እንዳይቀጣ፣
መንገዱም ቀጥታ ነው የሌለው አባጣ-ጐባጣ፤
ሁሉን የሚያለማ ሳይጓዳ እንዳንበጣ፣
እህልን የሚያጠፋ ከመሬት ተፈልፍሎ ሲወጣ።

Advertisements

%d bloggers like this: